#ETH

#ETH


በደኅንነት ሠራተኞች ላይ “የፖሊግራፍ” ምርመራ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሊውል ነው!

•ለደኅንነት ተቋሙ የሚሾም ሰው ከአምስት ዓመት በፊት የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልነበረ መሆን ይኖርበታል

•የመረጃ መረብ ደኅንነትና የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከልን ለማፍረስ ታቅዷል

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሚቀጠሩም ሆነ የሚመደቡ ሠራተኞች በተቋም ላይ የደኅንነት ሥጋት ወይም አደጋ አለማስከተላቸው ሲታመነበት ብቻ፣ እንዲቀጠሩ ወይም እንዲመደቡ የሚያስገድድና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ “በፖሊግራፍ” ቴክኖሎጂ የተደገፈ ምርመራ ሊደረግባቸው እንደሚችል ተገለጸ፡፡

ሪፖርተር በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ላይ የተጀመረውን ሪፎርም አስመልክቶ ከታማኝ ምንጮች ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሪፎርሙ ተጠናቆ ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር በተቋሙ የሚቀጠሩም ሆነ የሚመደቡ ሠራተኞች ላይ ጥብቅ የደኅንነት ማጣራት ይደረጋል፡፡

የደኅንነት ማጣራት ሒደቱን ውጤታማ ለማድረግም “የፖሊግራፍ” ምርመራ ጥቅም ላይ እንደሚውል ለማወቅ ተችሏል፡፡

“የፖሊግራፍ” ምርመራ ሐሰተኛ መረጃን ለመለየት የሚረዳ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ በዚህ ምርመራ ውስጥ የሚያልፉ ግለሰቦች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡበት ወቅት የሚስተዋልባቸውን አካላዊና ስሜታዊ ለውጦችን የምርመራ መሣሪያው በመመዝገብና በመተንተን የሰጡት መረጃ ሐሰተኛ መሆን አለመሆኑን ለመለየት የሚረዳ ነው፡፡

በዚህ ምርመራ ውስጥ የሚያልፉ ግለሰቦች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጡበት ወቅት ሊኖር የሚችልን በዓይን የማይታይ ስሜታዊና አካላዊ ለውጥ ለአብነት ያህል የልብ ምት ፍጥነት መጨመርን፣ የደም ግፊትና የአተነፋፈስ ሁኔታዎችን በመመዝገብና ለውጡን በመተንተን የሰጡት መረጃ ሐሰት መሆን አለመሆኑ እንደሚለይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በበርካታ የዓለም አገሮች ጥቅም ላይ የዋለ በመሆኑ፣ በተለይ በርካታ የአሜሪካ መንግሥት ተቋማት እንደሚገለገሉበት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በአሜሪካ ቴክኖሎጂውን ከሚጠቀሙ ተቋማት መካከል የአገሪቱ የአየር ኃይል፣ የመከላከያ ኢንተለጀንስ (ደኅንነት) ኤጀንሲ፣ ሴክሬት ሰርቪስ፣ ሲአይኤ፣ ኤፍቢአይና የኢነርጂ መሥሪያ ቤቱ ይገኙበታል፡፡

በደኅንነት ተቋም ሠራተኞች ላይ የሚደረገው የደኅንነት ማጣራት ትኩረት የሚያደርገው የወንጀል ሪከርድና የፋይናንስ ሪከርድ፣ ግለሰባዊ መረጃዎችን ለማግኘት ነው፡፡ በዚህም የግለሰቡን የደኅንነት ሥጋት ለመለየት ያለመ ነው፡፡ በተጨማሪም በሠራተኛው ለሚያዝ የኃላፊነት ቦታ የሚያስፈልገውን ታማኝነት ለማረጋገጥ፣ የደኅንነት ማጣራት እንደሚደረግ ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዕትም በዚህ የደኅንነት ተቋም ላይ ሊደረግ ስለታሰበው ሪፎረም ይዘቶች መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በዋናነትም የመረጃና ደኅንነት ተቋሙ ከማንኛውም ፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ በዚህም መሠረት በሕግ የተቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ፖለቲካዊ ዓላማ ለመደገፍ፣ ለማስፋፋት፣ ወይም ተፅዕኖ ለማሳደር መንቀሳቀስ እንደማይችል፣ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ በሚከናወኑ ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ወይም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ተግባራትን የመከታተልና የማጣራት ሥራ እንዳያከናውን በሕግ ገደብ እንዲጣልበት እንደሚደረግ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በተጨማሪ በተገኘው መረጃ ደግሞ ለተቋሙ በዋና ዳሬክተርነትና በምክትል ዳይሬክተርነት በመንግሥት የሚሾም ሰው ከመሾሙ ቀደም ብሎ በነበሩ የቅርብ ተከታታይ አምስት ዓመታት ውስጥ፣ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ ያላደረገና በግል ንግድ ድርጅት አመራርነትም ያላገለገለ መሆን እንደሚገባው መሥፈርት ሆኖ በሕግ እንዲቀመጥ መታቀዱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ይህም ማለት ለዚህ ተቋም የሚሾም ሰው ከመሾሙ አምስት ዓመት በፊት ባሉት ጊዜያት ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም የክልል ምክር ቤት አባል፣ ወይም የክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆኖ ያላገለገለ፣ በማንኛውም የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አመራር ያልነበረ እንዲሆን በመሥፈርትነት በሕግ እንዲቀመጥ መታቀዱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ ሪፎርም የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት የመረጃ መረብ ደኅንነት ጥበቃና የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ተግባራት እንዲያከናውን የታቀደ በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ይህንን ኃላፊነት እየተወጡ የሚገኙት የመረጃ መረብ ደኅንነትና የፋይናንስ ኢንተለጀንስ ማዕከል ኃላፊነታቸው ተዘዋውሮ እንዲፈርሱ ሊደረግ እንደሚችልም የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሪፎርሙም በዚህ ዓመት ከተጠናቀቀ በኋላ የሕግ ማዕቀፉም በፓርላማ ፀድቆ እንዲወጣና ተግባራዊ እንዲደረግ መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Via REPORTER

Report Page