#ETH

#ETH


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በጅቡቲ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ ዝግጅት ላይ በድንገት በመገኘት ንግግር አሰሙ

============

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን አስመልክቶ ቅዳሜ ዕለት (ጥቅምት 08፣ 2012ዓ.ም) በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት የተሰናዳ የደስታ መግለጫ ፕሮግራም ላይ በድንገት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓሉ ታዳሚ ለሆኑት ኢትዮጵያውያን ንግግር አሰምተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ‹‹ይሄ ግጥምጥሞሽ ነው… ዳያስፖራው ዝግጅት አለው ስባል ሰላምታ ለማቅረብ ነው የመጣሁት›› ብለዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ አክለውም ‹‹በጅቡቲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚለዩበት አንድ መለያ በሰላም መኖር፣ የአገሪቱን ህግ ማክበር፣ ስራ መውደድ፣ እርስ በእርስ መግባባት፣ የተቸገረን መርዳት ሲሆን ሁሌ የምትመሰገኑበትን ይሄንን መልካም ስማችሁን እንድታቆዩ አደራ እላችኋለሁ›› ብለዋል፡፡

ጅቡቲ ሁለተኛ ቤታችን ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ጅቡቲያውያኑ እኛን ይወዳሉ፤ እኛም ደግሞ አብዝተን እነሱን እንወዳቸዋለን ብለዋል፡፡ ዶ/ር አብይ መደመር በጅቡቲ እና በኢትዮጵያ በግልጽ መታዩት ጠቅሰው ይሄንን በሁለቱ አገራት መካከል ያለ ጥብቅ ወዳጅነት የምታጠናክሩ ድልድዮች ጀግና ኢትዮጵያውያን ስለሆናችሁ በታማኝነት፣ በጨዋነትና በፍቅር እዚህ ካለው ህዝብ ጋር በመኖር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማጠናከር እያንዳንዱ ዜጋ እንደ አምባሳደር እንዲሰራ አደራ ብለዋል፡፡

ስለ ኖቤል ሽልማቱ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማቱ በአንድ ሰው ስም መነገር ስላለበት እንጂ ሽልማቱ የሁላችሁም ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሰፋፊ ስራዎች መጀመሩን፣ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታላላቅ ኢኮኖሚ አንዷ እንድትሆን እየሰራ መሆኑን አክለው ገልጸው- የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የኤርትራ ብልጽግና መሆኑን አክለው ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም በውስጣችንም በአጎራባች አገራት ሰላም እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ከተመረጥን እንሰራለን ካልተመረጥን አቅፈን በማስረከብ አርዓያ የሆነ ስራ እንሰራለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ተሸንፎ ስልጣንን በስርዓት ማስረከብ ከዚህ ኖቤል የሚበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ስደት እንዲያበቃ ለልጆቻችን የምትበጅ ኢትዮጵያን ሰርተን ማቆየት አለብን በማለት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡

በጅቡቲ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉስልጣን አምባሳደር አብዱልአዚዝ መሐመድ በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገተኛ መገኘት የተሰማቸውን ደስታና ክብር ገልጸው በጅቡቲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አምባሳደሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለዚህ ታላቅ ዓለም-አቀፋዊ ሽልማት በመብቃታቸው በጅቡቲ የምንኖር እኛ ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ደስታ በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ሽልማቱ መላው ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ከመሆኑም ባሻገር አገራችን በዓለም-አቀፍ መድረኮች ላይ እየተጫወተች ያለውን ሚና የሚያጎላና እውቅናንም የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

በዝግጀቱ የተገኙት ኢትዮጵያውያን የተሰማቸውን ደስታና ክብር ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

( በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ )

Report Page