#ETH

#ETH


ባለፉት ሰባት ወራት ለሥራ ወደ ሌባኖስ ካቀኑ ኢትዮጵያዊያን መካከል ሰላሳ አራቱ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን እንዳጡ በሊባኖስ ያሉ የኢትዮጵያዊያንና ሌሎች የበጎ አድራጎት ማህበራት ይፋ አደረጉ።

ለኢትዮጵያዊያኑ ህይወት መጥፋት በአብዛኛው እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው በአሰሪዎቻቸው በሚፈጸምባቸው አሰቃቂ ግፍና ጥቃት ሳቢያ ራሳቸውን በማጥፋት እንዲሁም ካሉበት ኢሰብዓዊ የስቃይ ኑሮ ለማምለጥ በሚደርጉት ትግልና ጥረት እንደሆነም ተገልጿል።

ይህ ይፋ የሆነው በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እየገጠማቸው ያለውን አስከፊ ችግር በተመለከተ "መንግሥት የኢትዮጵያዊያን ሰራተኞችን ሞትና ስቃይን ለማስቆም" አፋጣኝ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ በጠየቁበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ላይ ነው።

"አስከሬን ወደ አገር ቤት መላክ ደከመን"

"አስከሬን ወደ አገር ቤት መላክ ደከመን" በማለት በደብዳቤያቸው ላይ ያሰፈሩት ኢትዮጵያዊያኑ በአገሪቱ ያለው ቆንስላ ጽህፈት ቤት ለዜጎቹ ደህንነትና መብት እየሰራ ባለመሆኑ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

"በኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ስላለው ግፍና ሰቆቃ በይገባኛል ስሜት አገርን ወክሎ በመንቀሳቀስ ረገድ በሌባኖስ ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ሙሉ ኃላፊነትም ሆነ ግዴታ ቢኖረውም፤ እውነታው ግን ፍጹም ከዚህ የራቀ ነው" በማለት በደብዳቤያቸው ላይ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ለሰባት ዓመታት ሊባኖስ ውስጥ ነዋሪ የነበረችውና ለችግር የተጋለጡ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት ከሚጥሩት አንዱን ድርጅት የምታንቀሳቅሰው ባንቺ ይመር ለቢቢሲ እንደተናገረችው "ይህ ነገር የቆንስላውን ስም ለማጥፋት የቀረበ ውንጀላ አይደለም" በማለት በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማሳወቃቸውን ገልጻለች።

ቆንስላው ዜጎቹን ለመርዳት ተገቢውን ጥረት ስለማያደርግ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ማህበራትን በመመስረት የቻሉትን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሳ፤ እሷም በየቀኑ ከአምስት በላይ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆነው እንደሚደውሉላት ትናገራለች።

"እኛ የምንችለውን ከማድረጋችን በፊት ቆንስላው ያጋጠሙ ችግሮችን እንዲያውቅና ድጋፍ ሲጠየቁ ለመስማት እንኳን ፈቃደኞች አይደሉም" ስትል ታማርራለች።

በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያዊያን ችግር ውስጥ መሆናቸውን በተመለከተ ሪፖርት ሲደረግላቸውና ሄደው ሲያገኟቸው፣ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ተባባሪዎች እንዳልሆኑና መረጃ ለማግኘት ስልክ በሚደወልበት ጊዜ ፈጽሞ መልስ እንደማይሰጡ ተናግራለች።

ቢቢሲም በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ላይ በኢትዮጵያውያን ላይ የቀረበውን ክስ አስመልክቶ በአራት መደበኛ ስልኮች ላይ በመደወል ለቀናት ምላሽ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ሦስቱ ስልኮቹ ቢጠሩም የማይነሱ ሲሆን አንደኛው ደግሞ በደንበኛው ጥያቄ መሠረት እንዲቋረጥ መደረጉን ለማወቅ ችሏል።

በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚበረታው በደል

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከሊባኖስ የሠራተኞች ሚኒስቴር የወጣን መረጃ ጠቅሰው እንደሚሉት ከ150 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። አክለውም ይህ አሃዝ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ያሉትን የሚያመለክት በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ህጋዊ ሳይሆኑ በአገሪቱ የሚሰሩ በመኖራቸው ቁጥሩ ከዚህ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጨምር ይገምታሉ።

በኢትዮጵያዊያኑ ላይ የሚፈጸመው ግፍ ከሌሎቹ የተለየ እንደሆነ የሚናገሩት እነዚህ ለሰራተኞቹ መብት መከበር የሚጥሩት ቡድኖች ከክፍያ አንስቶ በሊባኖስ የሠራተኞች ህግ ተጠቃሚ አይደሉም።

ኢትዮጵያዊያኑ በቀጣሪዎቻቸው፣ በአስቀጣሪዎቻቸውና ከሄዱበት መንገድ አንጻር የሌላ ሀገር ዜጎች እምብዛም የማይገጥማቸው ተጽእኖ እንደሚደረግባቸው በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ሊቀመንበር ሳሙኤል ተስፋዬ ለቢቢሲ ይናገራል።

"በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለምሳሌ መከፈል ያለበትን ዝቅተኛ ደሞዝ መጠን፣ አንድ ሰው ሊሰራ የሚገባውን የሥራ ሰዓትና የእረፍት ቀናቶችን የማግኘት መብታቸው ይጣሳል" ሲል ሳሙኤል ጠቅሷል።

ያልተገታው ህገወጥ ጉዞ

ከሁለት ዓመት በፊት የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው ከውጪ አገር መጥተው ሊባኖስ ውስጥ በሚሰሩ ሰዎች ላይ ከሚፈጸመው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ሰቆቃ በተጨማሪ በየሳምንቱ ሁለት ሰራተኞች ህይወታቸውን ያጣሉ። ከእነዚህ መካከልም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ይነገራል።

ይህ ሁሉ ስቃይ እየተሰማ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ወደ ሌባኖስ እየመጡ እንደሆነ ባንቺ ትናገራለች።

"ከሁሉ የሚያስደነግጠው ግን የሚፈጸመውን ግፍ ሳይሆን የሥራውን ጫና ለመሸከም የማይችሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መምጣታቸው ነው" በማለት ፓስፖርታቸው ግን ከ20 ዓመት በላይ እንደሆናቸው እንደሚያሳይ ትናገራለች።

ለዚህ ደግሞ የቀበሌ መታወቂያን በሐሰተኛ መንገድ ለማውጣት መቻላቸው ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ሳሙኤል አንስቶ ቤተሰቦችንንና በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉትን ይኮንናል።

"ምንም እንኳን ወደዚህ የሚገፋቸው ችግር ቢሆንም፤ ቤተሰብ ልጆቹን ሲልክ በምን ሁኔታ ወደየት እንደሚሄዱና ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል መረዳት አለበት" በማለት "ብዙዎች እዚህ ከመጡ በኋላ በሚገጥማቸው መከራና ጭካኔ እንኳን ለቤተሰባቸው ለራሳቸውም እንዳይሆኑ የሚያደርጉ ችግሮች ይገጥማቸዋል።"

ወደሊባኖስ በመሄድ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ለመለወጥ የወጡ በርካታ ኢትዮጵያዊን የሚገጥማቸው መከራ እንዳለ ሆኖ አንዳንዶች ደግሞ ደብዛቸው እንደሚጠፋ ባንቺ ትናገራለች።

"የሰሚ ያለህ"

"የት እንዳሉ ሳይታወቅ ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመታት በባርነት ያሉ፣ ድብደባ የሚፈጸምባቸው፣ የሚደፈሩ ሴቶችና ያለፍርድ እስር ቤት ያሉ አማራጭን ሲያጡ ራሳቸውን ለማጥፋት ይሞክራሉ" በማለት የግፍና ሰቆቃውን መጠን ትጠቅሳለች።

ከዚህ ባሻገር በሚፈጸምባቸው በደልና በሚያልፉበት ግፍና ሰቆቃ ሳቢያ ሥነ ልቦናዊ መረበሽ እየገጠማቸው ለሌላ የከፋ ጉዳት እንደሚዳረጉና ለዚህም በርካታ ምሳሌዎች እንዳሉ ሳሙኤልና ባንቺ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያውያኑ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዳሰፈሩት በሊባኖስ የሚደርስባቸውን መከራ ጉዳዬ ብሎ የሚከታተልና የሚረዳቸው የቆንስላ ጽህፈት ቤት እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

"በሊባኖስ ያለውን የኢትዮጵያ ቆንስላ የዜጎች ህመም የማይታየው በሚሰጠው መረጃ ፍጹም የማይታመን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዜጎች እንግልትና ስቃይ በሚደርስባቸው ግዜ የድረሱልን ጥሪ ሲያስተላልፉ ምንም እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የዜጎች ስቃይ ችላ የሚል ነው" ሲሉ አስፍረዋል።

ባንቺ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ለቢቢሲ እንደተናገረችው "በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ችግር በገጠማቸው ጊዜ ቆንስላው ይደርስልኛል ብሎ መጠበቅ ይቅርና አሉ ብሎ ማሰብም አይፈልጉም። ተጠሪ እንደሌለን ነው የምንቆጥረው" ትላለች።

የማይሰማው ጽህፈት ቤት

በአንዳንድ አጋጣሚዎች ቆንስላው ጣልቃ የሚገባበት ጊዜ ሲኖር ለዜጎቻቸው መብትና ደህንነት ከመቆም ይልቅ በአሰሪዎች ፊት ኢትዮጵያውያንን በማመናጨቅና በማዋረድ ወደነበሩበት የስቃይ ህይወት እንዲመለሱ እስከማስገደድ እንደሚደርሱ ባንቺ ትናገራለች።

በዚህ ሁኔታ ወደ አሰሪዎቻቸው የተመለሱ ሴቶች ሊገጥማቸው የሚችለው መከራና ጥብቅ ቁጥጥር ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ቀላል ነው የምትለው ባንቺ ከነዚህ ውስጥ ለባሰ ችግር የተዳረጉ ኢትዮጵያዊያንን እንደምታውቅ ትናገራለች።

"ቆንስላው በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን በተመለከተ አንዳንድ መረጃዎችን ከመሸፈን አልፎ፣ ጥቃት ስለተፈጸመባቸው እንዲሁም ስለተገደሉ ሰዎች በግልጽ የሚቀርቡ መረጃዎችን ማጣራትና መከታተል አይፈልግም። ማንም የሚጠይቃቸው የለም። ብዙ ጊዜ የሚገኙት የሞቱ ኢትዮጵያዊያንን ለመላክ ነው" በማለት ባንቺ በምሬት ትናገራለች።

ኢትዮጵያዊያኑ በደብዳቤያቸው በሊባኖስ ከሚገኘው ቆንስላ ማግኘት ሲገባቸው ስላላገኙት አገልግሎትና ተፈጸሙ ስለሚሏቸው በደሎች አስፍረዋል።

በዚህ ሁሉ መከራና ግፍ ውስጥ አሁንም በርካታ ኢትዮጵያውያን በህገ ወጥ መንገድ ወደሊባኖስ እየገቡ መሆኑን የሚናገረው ሳሙኤል፤ "በየዕለቱ የሚፈጸመው ሰቆቃና የምንሰማው ግፍ እየተባባሰ ነው። ከቆንጽላው በኩል የሚሰጠው መልስም ተስፋ አስቆራጭ ነው። ምንም መተማመኛ የለንም" ሲል የችግሩን መጠን መጨመር ጠቅሷል።

በተጨማሪም በሊባኖስ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት ለማስከበር የኢትዮጵያ መንግሥት ቆንጽላውን ወደ ኤምባሲ ከፍ እንዲያደርግና ለወገኖቻቸው የሚቆረቆሩና ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለሙያዎችን መድቦ ለመብታቸውና ለደህንነታቸው ዋስትና እንዲሆናቸው በመጠየቅ በደብዳቤያቸው ላይ መደረግ ያሉባቸውን ነገሮች ጠቁመዋል።

በሊባኖስ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ቤይሩት በሚገኘው የቆንስላ ጽህፈት ቤት ላይ ስላነሷቸው ጉዳዮች በስልክ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደዚያው ብንደውልም ስልኮቹ አይነሱም፤ በተጨማሪም አዲስ አበባ ከሚገኘው የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በቆንስላው ውስጥ ኃላፊ የሆኑ ግለሰብን ስልክ አግኝተን መልስ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

Via BBC

Report Page