#ETH

#ETH


በትናንትናው ዕለት የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አዳዲስ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል አልክም ማለቱን ተከትሎ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ለማለት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሥልጣን የለውም ሲል ለቢቢሲ ተናገረ።

ተማሪዎችን የመደበው የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ነው ያሉት በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ፣ ከመግለጫው በፊት በነበሩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ክልሉ ጥያቄውን ማቅረቡን ይናገራሉ።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ገ/መስቀል ካሕሳይ ትናንት እንደተናገሩት "ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ወደ ሚሰነዘሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እና ኃላፊነት ወደማይወስድ ክልል አዲስ ተማሪዎችን ላለመላክ የክልሉ አቋም ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የክልሉ አቋም ነው ያሉትን አማራ ክልል የተመደቡ 600 የሚደርሱ ተማሪዎችን ወደዚያ እንደማይልኩ ለሚመለከተው የፌደራል መንግሥቱ አካል ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

አቶ ደቻሳ ለቢቢሲ እንዳስረዱት ከትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በተደጋጋሚ በዚህ ጉዳይ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን ገልፀው፤ አሁን በክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ያለው ሰላም አስተማማኝ በመሆኑ ተማሪዎች ወደዚያው ሄደው እንዲማሩ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

"ሁሉም ተማሪዎች ወደየተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ሄደው ይማራሉ የሚል እምነት ነው ያለን" ያሉት ኃላፊው፤ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተጠሪነታቸው ለፌደራል መንግሥቱ በመሆኑ በየክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቢሮዎች ማዘዝ አይችሉም ብለዋል።

የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጨምረው እንዳሉት ዘንድሮ በአማራ ክልል ወደሚገኙ የትምህርት ተቋማት ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ከ2ሺህ በላይ እንደነበሩና ከሚመለከተው አካላት ጋር በተደረገው ንግግር ቁጥሩ ወደ 600 ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል።

ከትግራይ ክልል የቀረበውን ተከትሎም የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎችን በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ወደሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተመድበዋል፤ እነሱም ወደ ተመደቡበት ተቋም ሄደው መማር ያለባቸው ሲል አመልክተወል።

አቶ ደቻሳ ጉርሙ እንዳሉት "የስፖርትና የትምህርት ጉዳይ ሲነሳ በሁለቱ ክልሎች መካከል እንዲህ አይነት ክፍተት አለ" በማለት ከትግራይ በኩል የቀረበውን ሃሳብም "አንተገብረውም፤ ሊሆንም አይችልም" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያሉም ሆኑ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ እነዚህን ልጆች ተቀብለው አያስተናግዱም ያሉት ኃላፊው "የለባቸውምም" ሲሉ አስረግጠው ይናገራል።

ምክንያቱም ይላሉ ኃላፊው "ትግራይ ክልል ያሉትም ሆነ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች መቀበል በሚችሉት ልክ ተማሪ መድበናል" በማለት "ዩኒቨርስቲዎቹ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ተማሪ መቀበል አይችሉም፤ በጀትም የላቸውም" ብለዋል።

በዩኒቨርስቲዎች ዘላቂ ሰላም እንዲኖር፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው ያሉት አቶ ደቻሳ፤ እስካሁን ድረስ ያለው ሁኔታ ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የተሻለ አቀባበል ለተማሪዎች እየተደረገ ነው ያሉት የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተሩ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአካባቢዎቹ ማህበረሰብን አባላት የካተተበት ኮሚቴ በማቋቋም በቤተሰብ መንፈስ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን እየተቀበሉ መሆኑን ገልፀዋል።

Via BBC AMHARIC

Report Page