#eth

#eth


የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪችን አማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አልክም አለ!

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ገ/መስቀል ካሕሳይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡ "ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ወደ ሚሰነዘሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እና ኃላፊነት ወደማይወስድ ክልል አዲስ ተማሪዎችን ላለመላክ የክልሉ አቋም ነው" ብለዋል።

"አማራ ክልል የተመደቡት 600 ተማሪዎች እንደማይሄዱ ለሚመለከተው የፌደራል መንግሥት አሳውቀናል። ይህ የክልሉ አቋም ነው" ሲሉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።

ዘንድሮ፡ በትግራይ ክልል የዩኒቨሲቲ መግብያ ፈተና ወስደው ማለፍ የቻሉ የተማሪዎች ቁጥር ከ9000 በላይ መሆኑን የጠቀሱ ኃላፊው፤ ወደ አማራ ክልል ተመድበው የነበሩ ተማሪዎች ከ2000 በላይ እንደነበረ እና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ጋር በተደረገው ውይይት ወደ 600 ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።

"ከአንድ ወር ተኩል በላይ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሲወያይ ቆይቷል። የተቀሩ 600 ተማሪዎችን ሌላ ቦታ እንዲመደቡ ይሰራል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የትግራይ ክልል ሌላ አማራጭ ይፈልጋል እንጂ ተማሪዎቹን ወደዛ አይልክም" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲ አመዳደብ ስርዓት መሰረት ከአንድ ክልል አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በክልላቸው የተቀሩት 60 በመቶ ደግሞ ሌላ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ይመደቡ እንደነበረ የሚያስታውሱት ኃላፊው፤ "ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በበዙበት ወቅት ይህ ተቀይሮ 10 በመቶ በክልላቸው 90 በመቶ ደግሞ ወደ ሌላ ክልል እንዲላኩ መደረጉ አግባብ አይደለም" ብለዋል።

ይህ እንዲስተካከል ከፌደራል እና ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት መደረጉን እና 20 በመቶ በክልላቸው 80 በመቶ ደግሞ ከክልል ውጪ እንዲመደቡ መወሰኑን ጨምረው ተናግረዋል።

የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ገ/መስቀል ካሕሳይ ትግራይ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎች "ምንም አይነት የደህንነት ችግር አይገጥማቸውም" ብለዋል።

የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ሁለተኛ ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ተማሪዎች ዙሪያ ያሉት ነገር የለም።

BBC

Report Page