#ETH

#ETH


በትምህርት ተቋማት የሚስተዋል ዘረኝነት ተነቅሎ መጣል ይገባዋል - ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ

በየዩኒቨርሲቲዎችና ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ የጥላቻና የዘረኝነት አካሄዶች ህብረተሰቡን ያልሆነ መንገድ እንዲከተል እየደረጉት ስለሆነ ተነቅለው መጣል አለባቸው ተባለ፡፡ ይህ የተባለው በደብረብርሃን ከተማ ለ32ተኛ ጊዜ በተከበረው የመምህራን ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ ወቅት ነው፡፡

የአመራርና የመሪ ሚና በሚል መነሻ ሀሳብ ላይ የአነቃቂ ንግግር ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር ምህረት ሻንቆ እንዳሉት ትውልድ የመቅረፅ ስራ በዋንኝነት የሚወድቀው በመምህራን ላይ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትምህርት ቤቶች እንኳን ለሌላው ሊተርፉ ቀርተው ራሳቸው የፀብና የቁርሾ መፍለቂያ እየሆኑ ነው ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡

መምህርነት ራስን ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉ ከማህበረሰቡ ዕሴት ውጭ የሆኑ የዘረኝነት አካሄድን መምህራን ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ማስተካከል ለነገ የማይሉት የቤት ስራቸው ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በዕውቀት፣ በክህሎትና በስነምግባር ዘመኑን የሚመጥን ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት መምህራን እንደትላንቱ ሁሉ አገርን ለማሻገር የሚችል ትውልድ ለማፍራት ዛሬም መስዋዕትነት መክፈል የኖርባቸዋል ብለዋል።

እንደረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ በጉርብትናና በተለያየ ዝምድና አብሮ የኖረን ህዝብ እያጣላና እያለያየ ያለው በየዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች እየተዘራ ያለው መጥፎ ዘር ነው፡፡ እንዲህ ካሉ ችግሮች ለመላቀቅ ከመምህራን ብዙ ይጠበቃል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ መንግስት፣ ወላጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለመምህራኑ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

EPA

Report Page