#ETH

#ETH


የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ትላንት ባካሄደው 205ኛ መደበኛ ስብሰባው የመንግስት አስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ ጥናት፤ የደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት እና ከሲዳማ ብሔር ህዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ለማስፈጸም የሚያስችል የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ /ሞሽን/ እና ተጨማሪ በጀት ላይ በመወያየት ለክልሉ ምክር ቤት እንዲቀርብ ውሳኔ አሳተላልፏል፡፡

መስተዳድር ምክርቤቱ የመንግስት አስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት እንደገና ለማሻሻል የቀረበው ጥናት ለክልሉ ህዝብ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማስመዝገብ የተቋማትን አደረጃጀት የማስተካከል እና የመሰብሰብ ተግባር ዋናው ትኩረቱ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው ለማድረግ ሁለት መነሻዎችን ታሳቢ በማድረግ የተፈፀመ ነው፡፡

አንደኛው በሀገራችንና በክልላችን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ እንደመነሻ የተወሰደ ሲሆን ሁለተኛው የአስፈፃሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 178/2011 ትግበራ እንደመነሻ በመውሰድ የታየ ሲሆን በአስፈፃሚ አካላት መካከል የሚታየውን የቅንጅታዊ አሰራር መላላትና የተግባራት ድግግሞሽ በሚያስቀር ፣ ግልጽነትን ፣ ተጠያቂነትንና ፈጣን ምላሽ ሰጪነትን የሚያረጋግጥ የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ ለምክር ቤት እንዲፀድቅ ልኳል፡፡

በሁለተኛ አጀንዳነት የተመለከተው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት እና የሲዳማ ብሔር ህዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮችን ለመፍታት የቀረበ የውሳኔ ሀሳብ /ሞሽን/ ሰነድ ሲሆን ይህንን በጥልቀት ከገመገመ በኃላ የህዝበ ውሳኔ ሂደቱንና ውጤትን ተከትሎ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ በስፋት የመከረ ሲሆን የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማከል ለምክር ቤት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም በ2010 በጀት ዓመት ታውጆ በተለያዩ ምክንያቶች በስራ ላይ ያልዋለ በጀት እንዲሁም የህትመት ገቢ ፣ በበጀት ዓመቱ ከዕቅድ በላይ በተሰበሰበ ገቢ ፣ ከማሽነሪ ሊዝና ኪራይ እንዲሁም ከካሳ ክፍያ ገቢ ብር በጥቅል 527 ሚሊየን 269 ሺ 862 ለተለያዩ ወሳኝ የልማት ስራዎች እንዲውል ለምክር ቤት እንዲጸድቅ ልኳል፡፡

የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት

Report Page