#ETH

#ETH


ከመጪው ታህሳስ ወር ጀምሮ በኤሌክትሪክ ፍጆታ ላይ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ፡፡ ጭማሪው ለ4 ተከታታይ አመታት ተግባራዊ የሚደረገውና ባለፈው አመት የተጀመረው የታሪፍ ማሻሻያ አካል ነው ተብሏል፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ የታሪፍ ጭማሪ ከፍተኛ የሀይል ተጠቃሚ በሆኑ ደንበኞች ላይ ጫና እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡

ይህን የተሰማው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ2011 በጀት አመት የስራ አፈፃፀሙንና የ2012 እቅዱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ ነው።

ዝቅተኛ ሀይል የሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ሀይል በመቆጠብ የታሪፍ ጭማሪው ሊያመጣባቸው ከሚችለው ጫና ነፃ መሆን እንደሚችሉ በመግለጫው ተነግሯል፡፡

ባለፈው አመት ተግባራዊ በተደረገው የታሪፍ ጭማሪ ላይ በሕብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ቴክኒካል የሆኑ አሰራሮችን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች የግብአት አቅርቦት ችግርና የፋይናንስ እጥረት የተቋሙን ስራ ወደ ፊት ለማራመድ ችግር ፈጥሯል ያሉት የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ መላኩ ታዬ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ታሪፍ ማሻሻያው ይህን ችግር መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው በጀት አመት ኤሌክትሪክ ማግኘት የቻሉት ደንበኞች ብዛት ከእቅዱ 30 በመቶ ያልዘለለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ከ59 ሺ በላይ ደንበኞቹ ኤሌክትሪክ ለማግኘት ገንዘብ ከፍለው እየተጠባበቁ መሆኑን አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ምክንያት የሆነውን የግብአት አቅርቦት ችግር ለመፍታት የአገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን ለተቋሙ እንዲያቀርቡ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ስርቆቶች በተቋሙ ላይ ተጨማሪ ፈተና መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በ2012 የበጀት አመት 1 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ አለ ተብሏል፡፡

የሀይል መቆራረጥን ለመቀነስ የሚያግዙ የኔትወርክ ማሻሻያዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡

ምንጭ፦ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1

Report Page