#ETH

#ETH


በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ተጀምሮ የነበረው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ከኹለት ሳምንት በፊት እንዲቆም ተደረገ። ፈንዱ የቆመበት ምክንያትም እስካሁን በተዘዋዋሪ ፈንዱ የተሰጠውን ገንዘብ ለመለየት እንደሆነ ከተማ አስተዳደሩ ቢገልፅም ወጣቶች ግን ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

ከፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን ከሚጠብቁ ወጣቶች መካከል በ2011 በሲቪል ኢንጂነሪንግ የተመረቀው ዳዊት ተስፋዬ እንደሚለው “መንግሥት ተደራጅተን እንድንሠራ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚደርግልን ተነግሮን የሚጠበቁብንን ነገሮች በሙሉ አቅማችን አሟልተን፤ ከአንድ ወር በላይ እንደጠበቅን እና በተለይም በውድ ዋጋ የመሥሪያ ቦታ ተከራይተን ከፍተኛ ወጪ ላይ ብንሆንም ፈንዱ ግን ሊለቀቅልን አልቻለም” ሲል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የቄርቆስ ክፍለ ከተማ ማስተባበርያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኦፕሬሽን ኀላፊ አለኸኝ ከበደ እንደተናገሩት የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ባለፉት ኹለት ሳምንታት ውስጥ እንዲቆም የተደረገበት ምክንያት እስካሁን በየክፍለ ከተማው ለምን ያህል ሰዎች ምን ያህል ገንዘብ ለወጣቶቹ ተሰጥቷል የሚለውን ጥናት ለማድረግ ነው። እስካሁንም 1.6 ቢሊዮን ብር የተሰጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ለኢንትርፕራይዞቹ ድጋፍ እንዲሆን የቀረው ገነዘብ ግን 400 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል።

አያይዘውም በዚህም የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድሩን አግኝተው ወደ ሥራ የገቡ ወጣቶች ሲኖሩ በሌላኛው ጎን ደግሞ በሒደት ላይ የሚገኙ ወጣቶች ብዙዎች ናቸው። በክፍለ ከተማውም 392 ኢንተርፕራይዞች ውሳኔ አግኝተው ሥራ የጀመሩ ሲሆን 309 ኢንተርፕራይዞች አገልግሎቱን ለማግኘት እየጠበቁ ነው ብለዋል።

ሆኖም ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ቅድሚያ ይሰጣቸው ብሎ ያስቀመጣቸው ወጣቶችን ፋይል ክፍለ ከተማ በማስገባት ብድሩን እየተጠባበቁ ሲሆን አገልግሎቱም በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል ብለዋል።

“የንግድ ቤት ለመከራየት ኹለት አማራጭ ነበረን ራሳችን በተደራጀንበት ወረዳ ውስጥ ቤት ፈልገን ቤት መከራየት ሲሆን ይህ ደግም ሥራ አጥ ስለሆንንና ብርም ማግኘት ስለማንችል አስቸጋሪ ነበር” ሲል ዳዊት ስላጋጠመው ወጪ ይናገራል። “ኹለተኛው አማራጭ የንግድ ቤቱ ከተገኘ በኋላ መንግሥት ይከፍልልናል ተብሎ መከራየት ነበር፤ ሆኖም ግን መንግሥት የሚከፍልበት ዕድል በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ አከራዮች አይቀበሉትም። በመሆኑም ይህንን ሒደት ለማፋጠን ቤት ከተከራየን በኋላ ነው የብድር አገልግሎቱ ቆሟል የተባለው። ክፍለ ከተማ ብናመለክትም ከከተማ አስተዳደሩ በመጣ ድበዳቤ እንዲያቆሙ መደረጉን ከመናገር ውጪ መፍትሔ እንደሌላቸው ነግረውናል። ይህ ተገቢ አይደለም አሁንም ቢሆን መንግሥት በቃሉ መሰረት ድጋፍ ማድረግ አለበት።”

መንግሥት የወጣቶች ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎችን አደራጅቶ በማስገባት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማጎልበት የሚያስችል የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ 10 ቢሊዮን ብር መመደቡና በ2009 ተግባራዊ መደረጉ የሚታወስ ነው። በፈንዱ የተቀመጠውም 10 ቢሊዮን ብር የየክልሉን ወጣቶች ብዛት መሰረት በማድረግ በየክልሉ እንዲከፋፈል የተደረገ ሲሆን በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በቅርቡ ለወጣቶች በመደበው የ2 ቢሊዮን ተዘዋዋሪ ፈንድ የተለያዩ ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል።

ፈንዱ እንዲቆም መደረጉ ዋነኛ ምክንያት እስካሁን ለኢንተርፕራይዞች የተከፈለ ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ እና አሁን በሒደት ላይ ላሉ ኢንተርፕራይዞች ቀሪ ክፍያ የሚሆነውን ጥናት አድርጎ ለመለየት ነው ተብሏል።

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ከኹለት ሳምንት በፊት እንዲቆም መደረጉ በዚህ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ተጠቃሚ ለመሆን ሙሉ አቅመማችንን እንዲሁም ገንዘባችንን አውተናል የሚሉት ወጣቶች፤ መንግሥት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላችዋል ብሎ ከየቤታችን አስወጥቶ መሥራት እንደምንችል መንገዱን በመክፈቱ ዕድለኞች ነበርን።

ሆኖም ግን ሥራ ለመጀመር ካለን ፍላጎት የተነሳ ከቤተሰቦቻችን እና ከተለያዩ ሰዎች ብድር በመውሰድ የቤት ኪራዩን በራሳችን ከፍለናል፤ ይህን ሒደት ካለፍን በኋላ እና እያንዳንዳችን ያለንን ጊዜና ገንዘብ አውጥተን ዝግጁ በሆንበት ወቅት ይህ ነገር መፈጠሩ ተገቢ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

Via Addis Maleda

Report Page