#ETH

#ETH


ነገር ሲደጋገም ይሰለቻል! ግን እውነታው ይሄ ነው…

በተመላላሽ ህክምና ክፍል የጡት ካንሰር እንዳለባቸው የሚነገራቸው ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም… አይነተኛ የጡት ካንሰር ምልክቶችን የማያውቁ ነገሩ ከረፈደ በኋላ ወደጤና ተቋማት የሚመጡ ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም…የጡት ካንሰር የሞት ፍርድ እንደሆነ የሚያስቡ ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም… ነገር ሲደጋገም ይሰለቻል… ግን ማህበራዊ ገጾችን ትምህርት ልንሰጣጥባቸው እንችላለን… ነገር ሲደጋገም ይሰለቻል… ግን እርስዎም ሀላፊነት አለብዎት… ነገር ሲደጋገም ይሰለቻል ግን ቮልቴር እንዳለው ላላደረጉት መልካም ነገር ሁሉ ወዳጄ ሆይ ተጠያቂ ነዎት!! እናም ይስሙ! ላልሰማም ያሰሙ!!

የጡት ካንሰር በጡት የሚገኙት ህዋሳት ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልክ ሲራቡ የሚፈጠር ነው፡፡ በሀገራችን በሴቶች ላይ ከሚፈጠሩ የካንሰር አይነቶች የጡት ካንሰር አንደኛ ደረጃውን ይይዛል፡፡ አጋላጭ ሁኔታዎች ተብለው ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች፡

ጾታ (ከወንዶች ይልቅ ሴቶች 99 ፐርሰንት ያህል የመያዝ እድል አላቸው፡፡)

እድሜ (በለጋ እድሜ ያሉ ማለትም ከ20 አመት በታች ያሉ ተጋላጭነታቸው ያነሰ ሲሆን እድሜ በጨመረ ቁጥር በበሽታው የመያዝ እድል ይጨምራል፡፡)፣

በቤተሰብ ያለ የጡት ካንሰር (የተለያዩ በቤተሰብ የሚተላለፉ የዘረመል ግድፈቶች ለጡት ካንሰር ሊያጋልጡ ይችላሉ)

እብጠት (የመጓጎል ስሜት ያለው)፣ የጡት ጫፍ ወደውስጥ መግባት፣ የጡት ጫፍ መድማት፣ ያልተለመደ አይነት ፈሳሽ ከጡት መውጣት የጡት ካንሰር ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ እነኚህን ነገሮች እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው ካስተዋለ እባክዎ ወደጤና ተቋም ለመሄድ አያቅማሙ፡፡ ምልክቶችን ገና በጊዜ ማወቅ እንዲችሉ ጡትዎትን በደንብ ይወቁት፡፡ በወር አንድ ጊዜ በእጆችዎ ጡትዎን በመፈተሽ የጡትዎን ጤንነት ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ፍተሻው የወር አበባ ባለቀ በሳምንቱ ቢሆን ይመከራል፡፡ የወር አበባ ማየት ያቆሙ ሴቶች በማንኛውም ጊዜ ይህንን ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በሚከተለው መንገድ ፍተሸውን መተግበር ይቻላል፡፡

ሀ. መመልከት

በመስታወት ፊት ይቁሙ፡፡ ሁለቱንም እጅዎትን ወደላይ በማድረግ ጡቶችዎን ይመልከቱ፡፡ የቀለም መለወጥ፤ ስርጉዳት ወይም የሚወጣ ፈሳሽ ካለ ያስተውሉ፡፡ ካሻዎት ጡቶችዎን ከፍ በማድረግ ቆዳዎን ይመልከቱ፡፡

ለ. መንካት

በጀርባዎት ይንጋለሉ፡፡ ግራ እጅዎን ከጭንቅላትዎ ጀርባ በማድረግ በቀኝ እጅዎ የግራ ጡትዎን ይዳብሱ፡፡ በብብትዎ በኩል በላይ ካለው የጡት ክፍል በመጀመር ልክ ሰዐት እንደሚሄደው ጣቶችዎን በማሽከርከር የጡትዎን ሁሉንም ክፍል ይዳብሱ፡፡ በሶስት ዙር ይዳብሱ፡፡ በመጀመሪያ በስሱ፤ ቀጥሎም ጫን በማለት፡፡ በመጨረሻም በኃይል በመጫን፡፡ እባጭ ወይም ስርጉዳት ወይም የቆዳ መቀረፍ ካለ ያስተውሉ

የጡትዎን ጫፎች በመጭመቅ የሚወጣ ፈሳሽ ካለ ያስተውሉ፡፡

እጅዎን በመቀየር በተቃራኒው ጡትዎት ይህንኑ ይድገሙ፡፡

በጀርባዎ መንጋለልዎ ጡትዎን በቀላሉ መፈተሸ እንዲችሉ ያደርጎታል፡፡ ቆመውም ቢሆን ይህንን ፍተሸ ማድረግ ይችላሉ፡፡ 

በቤተሰብ የጡት ካንሰር ታሪክ ያላቸው እድሜያቸው ከ40-49 ያሉ ሴቶች እንዲሁም እድሜያቸው ከ50 በላይ የሆኑ ማንኛውም ሴቶች በቴክኖሎጂ የታገዘውን የማሞግራም ምርመራ በአመት አንድ ጊዜ እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡ 

እባክዎ ይህንን መልእክት ለሚወዷቸው እና ለሚወድዎት ይላኩ! የነጮቹ ኦክቶበር የጡት ካንሰር ግንዛቤ መስጫ ወር ነው፡፡ እርስዎም ሴቶችን ከዚህ በሽታ ለመታደግ የበኩልዎን አስተዋጽኦ ያድርጉ፡፡

Via LOZA

Report Page