#ETH

#ETH


በአገሪቱ እስካሁን ድረስ በተካሄዱ አምስት ዙር ጠቅላላ ምርጫዎች ፍፃሜና ክንውን ጋር በተገናኘ ከተለያዩ የዘርፉ ተዋናዮች፣ ከገለልተኝነት አንፃር በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን ተዓማኒነትን ለማረጋገጥና መጪው የ2012 ዓ.ም. ምርጫ ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ ቦርዱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ከባለድርሻ አካላት ጋር ከሚደረገው ውይይት ባሻገር ግን ቦርዱን በሰብሳቢነት እንዲመሩ ባለፈው ዓመት የተመረጡት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የበርካታዎችን ይሁንታ ማግኘታቸው በራሱ የቦርዱን ተዓማኒነትና ነፃነትን ለመጎናፀፍ የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ወ/ሪ ብርቱካን የቦርዱን ሰብሳቢነት ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ የወጡት አዋጆች በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጁ ግን በዋነኛ ባለድርሻ አካላት ማለትም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በቦርዱ መካከል የነበረውን አለመተማመን መልሶ ያመጣው ይመስላል፡፡

አዋጁን በመቃወም በርካታ ፓርቲዎች የተለያዩ መግለጫዎችን ሲያወጡ የነበሩ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ አዋጁን ለመቃወም የተሰባሰቡ 70 ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ የረሃብ አድማ ለማድረግ እንዲሁም በመላው አገሪቱ የተቃውሞ ፊርማ ለማሰባሰብ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቀጣዩን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን ሥራውን መጀመሩን የሚገልጸው ቦርዱ፣ ምርጫውን የተሳካ ለማድረግ በማለም የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የዚህ የባለድርሻ አካላት ውይይት አካል የሆነውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ‹‹አገራዊ ምርጫና የምርጫ ባለድርሻ አካላት ሚና›› በሚል ርዕስ ማክሰኞ መስከረም 27 እና ረቡዕ መስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ አከናውኖ ነበር፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሕጉን አሻሽሎ፣ ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅቱን በጀመረበት ወቅት ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ገንቢና መልካም የሆነ ትብብር በምርጫ ቦርዱ ላይ ለሚኖር መተማመንና ሕዝባዊ ተዓማኒነትን ለማስፈን ወሳኝ እንደሆነ ቦርዱ እንደሚረዳ በኮንፈረንሱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳካት ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር በተለያዩ መድረኮች ውይይት ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል፡፡

ይህ ለሁለት ቀናት የቆየውና በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመክፈቻ ንግግር የተከፈተው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ የተለያዩ ወሳኝ ባለድርሻ አካላት የታደሙበት ሲሆን፣ የቀድሞ የናይጄሪያና የዛምቢያ የምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ልምዶቻቸውን አካፍለውበታል፡፡

የኮንፈረንሱ ዓላማዎችና ግቦችም ተመሳሳይ ተሞክሮዎችና አመለካከቶች ያላቸውን አገሮች ልምድ በማየት ችግሮቻቸውን በውጤታማ መንገድ የፈቱባቸውን መንገዶች መጋራት፣ ከቁልፍ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖር የትብብርና የቅንጅት ዕቅድን መንደፍ፣ ከምርጫ ሒደቱ ማሻሻያ ጋር እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችንና ከምርጫ ዝግጅነቱ ጋር ያሉ ወሳኝ ምዕራፎችን ማሳወቅ፣ እንዲሁም ስለምርጫው ሒደትና የፀጥታ ችግሮችን በተመለከተ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መወያየት የሚሉ ነበሩ፡፡

ከዚህ አንፃር የናይጄሪያና የዛምቢያ የቀድሞ የምርጫ ኮሚሽነሮች በየአገሮቻቸው ያጋጠማቸውን ከምርጫ ጋር የተያያዙ ተሞክሮዎችን ያጋሩ ሲሆን፣ ሌሎች ጽሑፎችም ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል፡፡

በተለይ ለሁለተኛው ቀን የኮንፈረንሱ ውሎ ላይ ምርጫውን ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር ያሉ ሥጋቶችና መልካም አጋጣሚዎችን አስመልክቶ በቀድሞ የኢፌዴሪ አየር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዓለም እሸት ደግፌ የቀረበው መነሻ ሐሳብ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከተለያዩ ማዕዘኖች የቃኘና ምርጫውን ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር ቦርዱም ሆነ መንግሥት ሊተገብራቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የቀረበ ምክር አዘል ማሳሰቢያ ነበር፡፡

ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ የፀጥታ ሥጋቶች ወይም ችግሮች መንስዔዎቹ ምን ምን ናቸው? ከዚህ አንፃር ተጨባጭ አደጋዎች የምንላቸው እንዴት ያሉትን ነው? እነዚህን ሥጋቶች ወይም ችግሮች ለመቋቋም አሊያም ለመቆጣጠር ያሉን አቅሞች ምን ምን ናቸው? በሚሉ ዓበይት ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን የሰነዘሩት ጡረተኛው ሜጀር ጄኔራል ዓለም እሸት በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ትንታኔም ሰጥተዋል፡፡

‹‹ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን መሥራት ይገባቸዋል፤›› በማለት በመግለጽ፣ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሊነሱ የሚችሉ የሰላም ሥጋቶችን ከፖለቲካዊ፣ ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ከደኅንነት ጉዳዮች አንፃር በመመልከትና በመተንተን መፍትሔ ያሉትን ሐሳብም አቅርበዋል፡፡

ሜጀር ጄኔራል ዓለም እሸት እንደ ሥጋት ምንጭነት ከገለጿቸው አራት ምክንያቶች መካከል የፖለቲካ ሥጋቱ ዝርዝር የሆነ ማብራሪያ የቀረበበት ሲሆን፣ በእርግጥም በዚህ ዘርፍ የሚነሳውን ሥጋት በቅጡ አዳምጦ መፍትሔ መስጠት ለቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ለአገራዊ አንድነትም ሆነ ሰላምና መረጋጋት የሚጫወተው ሚና ዓይነተኛ ነው፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ የፖለቲካ ሥጋትን ሊያባብሱ አሊያም ችግር እንዲሆን የሚደርጉት ምክንያቶች የሰብዓዊ መብትን አለማክበር፣ የሕግ የበላይነትን አለማክበርና እንዲከበርም ቁርጠኛ አለመሆን፣ በሁሉም መስክ የሚታየው ዴሞክራሲ ባህል አለመዳበርና ጉድለት፣ አገራዊ ዕርቅ የሚለው ሐሳብ ላይ መግባባት ላይ አለመደረሱ፣ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ስምምነት ላይ አለመደረሱ፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄ፣ በትጥቅ ትግል መቀጠል የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች እዚህም እዚያም መኖር የሚሉት ናቸው፡፡

በዚህ ዘርፍ በተለይ የዴሞክራሲ ባህላችን አለመዳበርና ጉድለትን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ ‹‹በዚህ ጉድለት የተነሳ በምርጫ ሥልጣን መያዝን አለመቀበል ይስተዋላል፤›› በማለት፣ ከአገሪቱ የፖለቲካ ባህልና አደባባይ ላይ ተመቻምቾና ነገን አልሞ በምርጫ ተወዳድሮ ዳግም ማሸነፍ እንደሚቻል አለማሰብ ጉድለት መሆኑን አውስተዋል፡፡

በተያያዘም አገራዊ ዕርቅና መግባባት ላይ ለመድረስ አለመቻሉ ምርጫውን ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የገለጹ ሲሆን፣ ይህንን ወደ መሀል አምጥቶ ሊያግባባ አሊያም ሊያደራድር የሚችል የሽማግሌዎች መማክርት እንኳን የለም በማለት፣ ይህም አሉታዊ ጥላውን ሊያጠላ እንደሚችልና ሊታሰብበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ የሰላም ችግር መንስዔ ሊሆን የሚችለውን አስመልክተው ደግሞ፣ በተለይ በአገሪቱ የሀብት ክፍፍል ፍትሐዊ አይደለም ከሚል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የይገባኛል ጥያቄዎችን መፍትሔ በመስጠትና ከዚህ አንፃር ዘላቂ መፍትሔ ላይ ካልተደረሰ የችግር ምንጭ በመሆን ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ አውስተዋል፡፡ 

በመሆኑም በፖለቲካው መስክ አገራዊ መግባባት በመፍጠር፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አመቺ ሥርዓት መዘርጋት፣ ከምርጫ ጋር ተያይዞም ሆነ ሌሎች ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ መሥራት እንደሚቻልና እንደሚገባም ምክር ለግሰዋል፡፡

በማኅበራዊ ዘርፍ የግጭት መንስዔ ሊሆን የሚችለውን ሲገለጹ ደግሞ፣ በዋነኛነት በጽንፈኛ ኃይሎች አማካይነት የሚነሱ የበዳይ ተበዳይ ትርክት፣ የሃይማኖቶች ፉክክር፣ እንዲሁም የሕዝብ ቁጥር መጨመርን እንደ ማሳያነት አንስተዋል፡፡

በተለይ የሕዝብ ቁጥር መጨመሩ የሥራ አጡን ቁጥር በዚያው ልክ ስለሚጨምረው ይህም ሊጤን እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር ለአገር አለመረጋጋትና የግጭት መንስዔ እንደሚሆን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሱ ሕዝባዊ አመፆች ላይ ተካፋይ የነበሩ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችን ማስታወስ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

የደኅንነት ሥጋት መንስዔን በተመለከተ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ትጥቅ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖርና ለምርጫው ሲባል ሕዝብን በአንድ ሥፍራ ማስፈር አሊያም ከአንድ ሥፍራ ማፈናቀል የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ከሚሰማው የሕገወጥ መሣሪያ ዝውውር መጨመር ጋር ተያይዞ፣ ችግሩን ለመቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ በጊዜ ካልተዘረጋ በስተቀር ከፍተኛ የደኅንነት አደጋ ሊሆን እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት የሰላም የሥጋት መንስዔዎች አንዳንዶቹ በሒደት ሊፈቱ የሚችሉ ቢሆንም፣ በአፋጣኝና ምርጫው ከመካሄዱ በፊት መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገባ እንዳሉም መክረዋል፡፡ በተለይ የሕገወጥ የጦር መሣሪ ዝውውርን፣ እንዲሁም በተወሰነ ቦታ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎችን አስመልክቶ የተገለጹት አፋጣኝ መፍትሔ የሚሹ ናቸው በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጣዊ ሥጋቶች በተጨማሪ ከውጭ ሊገጥሙ የሚችሉ ሥጋቶችን የገለጹ ሲሆን፣ አንዳንድ በርቀት ያሉ አገሮችም ይሁን ጎረቤቶቻችን ምርጫውን ተጠቅመው አገሪቱን ለማተራመስ ሊሠሩ ይችላሉ በማለት የአገሮቹን ስም ሳይጠቅሱ፣ ነገር ግን ከዚህ አንፃር ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እነዚህ በስም ያልተጠቀሱ የውጭ ኃይሎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ለምሳሌ የተቃውሞ ሠልፍ፣ ሥራ የማቆም አድማ፣ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይጠናከሩ ወጣቶቻን በማስታጠቅና በመጠቀም ምርጫውን ለመበጥበጥ ሊሠሩ እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ከላይ የተገለጹትን ሥጋቶች ከመከላከል አንፃር ያሉንን አቅሞች ሲገልጹ ደግሞ፣ በዋነኛነት መከላከያው፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስና ሚሊሻዎች አቅሞች ናቸው በማለት የገለጻቸው ሲሆን፣ ነገር ግን ምርጫውን ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር እነዚህ አካላት የምርጫውን ፀጥታና ሰላም መጠበቅን የተመለከተ ሥልጠና ሊሰጣቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

እነዚህን አቅሞች ለመጠቀም ደግሞ አንድ የምርጫ ፀጥታ ማስከበር ማስተባበሪያ ማዕከል እንዲቋቋም የመፍትሔ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ይህ ማዕከል የመከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት አባቶችና የቦርዱ ተወካዮች ያሉበት አባላት እንዲኖሩትና ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ እየተሰበሰበ መረጃዎችንና ሥጋቶችን በመተንተን ወደ ግጭት ሳያመሩ ለመቆጣጠር የሚስችል ሥራዎችን እንዲሠራ ማደራጀት ያስፈልጋል በማለት ገልጸዋል፡፡

ይህ ማዕከል ሁለት ንዑስ ክፍል ይኖረዋል፡፡ እነዚህም መረጃ የሚሰበስብና የሚተነትን እንዲሁም የሥምሪት ማዕከል ሲሆኑ፣ የእነዚህ ተቀናጅቶ መሥራት የሥጋት ቀጣናዎችን በመለየትና አፋጣኝ መፍትሔዎችን ለመውሰድ ለሰላም መደፍረስ ሥጋት የሚሆኑ ምንጮችን የማድረቅ ሥራ መሥራት እንደሚቻልም ምክረ ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

ምርጫ 2012ን ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር የተሰነዘሩ ሐሳቦች በጣም ጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ ግን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ የሁሉም ተሳትፎ እንዲቀጥል ጥሪቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ይህም ምርጫ መሳካቱ ግዴታችን መሆኑን አምነን ወደ ምርጫው ከገባን ምርጫውን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ስኬታማ ማድረግ ይቻላል፤›› በማለት፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለምርጫ 2012 ዓ.ም. መሳካት ወገቡን ጠበቅ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለመካሄድ የወራት ዕድሜ የቀረው የ2012ቱ ጠቅላላ ምርጫ ከፊቱ በርካታ ፈተናዎች የተደቀኑበት ቢመስሉም፣ ምርጫው ውጤታማ እንደሚሆን ተስፋ የሚያደርጉም አሉ፡፡ የምርጫውን አጠቃላይ ድባብ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት የምንመለከተው ይሆናል፡፡  

#reporter

Report Page