#ETH

#ETH


የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያውያን ተስፋ ለአገር መሪዎች እና ለሲቪክ ማህበራት ቃል ኪዳን መሆኑን በሳውዝ ኢስት ኖርዌይ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ግሩም ዘለቀ ገለጹ፡፡

ዶክተር አብይ የኖቤል ተሸላሚ እንዲሆኑ ጥቆማ ያደረጉት ዶክተር ግሩም ከኖርዌይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬ እንደተናገሩት፤ ዶክተር አብይን መከታተል የጀመሩት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ነበር፡፡ ከተሾሙም በኋላ እያንዳንዱን ንግግራቸውን እና ተግባራቸው ሲከታተሉ ቆይተዋል፡፡

እንደ ዶክተር ግሩም ገለጻ፤ ዶክተር ዓብይ ለሰው ልጆች ያላቸው አክብሮት ፣ሰላማዊ መሆናቸው ፣እጅግ በጣም የሚማርክ ሰብዕና ያላቸውና የሚያስገርሙ መሪ ናቸው። ይህ ስብዕናቸው ስለማረካቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኖቤል እጩ እንዲሆኑ መጠቆም እንዳለባቸው ሊወስኑ በቅተዋል፡፡

"ዶክተር ዐብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ አንድ ሰው በሚሰራው ስራ መመስገን አለበት እንደሚሉት እኔም ሁሌም ሰው ሲያጠፋ ብቻ ከመውቀስ ይልቅ ሲሰራም ማበረታታት ያስፈልጋል በማለት ለዕጩነት ለማቅረብ ሰርቻለሁ" ብለዋል ዶክተርግሩም።

ዶክተር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ እጅግ የሚያስመሰግን ስራ ስርተዋል የሚሉት ዶክተር ግሩም፤ ከሰሯቸው አያሌ ስራዎች መካከል በተለይ ግጭትን በመፍታት ዙሪያ ማለትም ሰዎች በእኩል አይን መታየት እንዳለባቸው ፣ ለይቅርታ መስራታቸውና ፣ኅብረተሰቡን ለማረጋጋት የሚያደርጓቸው ንግግሮች በመሪ ደረጃ በታሪክም ከነበሩ መሪዎች እንደሚለዩ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ዓብይ ባላቸው የፍልስፍናም ሆነ የተግባር ዕውቀት ሽልማቱ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ፤ ያሉት ዶክተር ግሩም በዚህም ምክንያት ነው ለዕጩነት ለማቅረብ ስሰራ የነበረው ብለዋል፡፡ ለዕጩነት የማቅረብ ስራውም አንድ ዓመት እንደፈጀባቸው ጠቁመዋል፡፡

እንደ ዶክተር ግሩም ገለጻ፤ ዶክተር ዓብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያደረጉትን ንግግሮች ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎም የግል ሀሳባቸውን በማከል ለዕጩነት ለማቅረብ 61 ገጽ ደጋፊ ጽሑፎችን አዘጋጅተዋል፡፡

ለጥቆማ የተጠቀምኩት ከደብዳቤ ባሻገር አብዛኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ፊት ያደረጓቸውን ንግግሮች ነው ያሉት ዶክተር ግሩም፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ደግሞ ከአልፍሬድ ኖቤል የመመዘኛ ነጥቦች ወይም ማመሰካሪያዎች ጋር የሚገናኙ በመሆናቸው ለድጋፍ እንደተጠቀሙበት ተናግረዋል፡፡

"እንደ ዶክተር ዓብይ ዓይነት መሪ ማግኘት እጅግ ይከብዳል። በዓለምም ያሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። ታዲያ እንዲህ ያለ መሪ በዓለም ትልቅ የሆነ ሽልማት ሲሸለም በጣም ነው የሚያስደስተው፡፡ እኔ እራሴ መጀመሪያ ዜናውን ስሰማ አላመንኩም ነበር፡፡ እንደገና ወደኋላ በመመለስ ካዳመጥኩኝና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ካየሁ በኋላ ነው እውነት መሆኑን ያወቅኩት" ብለዋል፡፡

Via EPA

Report Page