#ETH

#ETH


የሸቀጦች የዋጋ ንረት መቋቋም እንዳልቻሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገልጹ!




ጥቅምት 1/2012 በፍጆታ ምርቶችና እቃዎች ላይ በሚታየው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ መቸገራቸውን የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

የክልሉ ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ በበኩሉ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑ አስታውቋል።

ኢዜአ የዋጋ ንረቱን አስመልክቶ ካነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች መካከል የሃውልት ክፍለ ከተማ ነዋሪ መምህር ዓብደልቃድር አውዱ እንዳሉት በከተማው ውስጥ በአገልግሎትና በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት እጅግ የተጋነነ ነው።

ከዋጋ ንረቱ በተጨማሪም የሽቀጦች እንደልብ አለመገኘት ሌላ ችግር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

”በከተማው የሚገኙ ሕገ ወጥ ደላሎችም በሸቀጦቹ ዋጋ መጨመር የራሳቸው አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው” ብለዋል መምህር ዓብደልቃድር።

መንግስት እየተባበሳ ያለውን የኑሮና የቤት ኪራይ ውድነት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ካልተረባረበ የኢኮኖሚ ቀውስ ይከሰታል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ገልፀዋል።

በመቀሌ የዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ተስፋይ በበኩላቸው የምርት ዋጋ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም ብለዋል።

ቀደም ሲል 2ሺህ 300 ብር የነበረ አንድ ኩንታል አንደኛ ደረጃ የጤፍ ምርት ወደ 3ሺ300 ብር ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

600 ብር የነበረ 25 ኪሎ ግራም የዳቦ ድቄት ደግሞ እስከ 800 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።

አንድ እንጀራ ደግሞ ከሰባት ብር ወደ 11 ብር ማሻቀቡን ገልፀው አንድ ብር ከ25 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ አንድ ዳቦ ደግሞ ዛሬ ላይ ሁለት ብር መድረሱን ተናግረዋል።

”በሸቀጦች የዋጋ መናር ምክንያት ቁርስና ምሳ ለመብላት እየተቸገርኩ ነው” ያለው ደግሞ በከተማው የሐድነት ክፍለ ከተማ ነዋሪ እና በግንበኝነት ሙያ የተሰማራው ወጣት አምሳሉ ታረቀ ነው።

በተለይ ህገ ወጥ ደላሎች በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ በየጊዜው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይ እያደረጉ መሆኑን ገልፆ እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግስትና ህዝብ የተቀናጀ ስራ መስራት አለባቸው ብሏል።

የትግራይ ክልል ንግድ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ፋንታሁን ስለጉዳዩ ተጠይቀው እንዳሉት በሸቀጦች ላይ የሚታየውን የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ አፋጣኝ ምላሽ የሚሻው ነው ብለዋል።

”የችግሩ ዋና ምክንያት የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ነው” ያሉት አቶ ሃፍቶም የተገኘው ምርትም በህግና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዳይከፋፈል የህገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች ሚና እየገዘፈ መምጣት ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል።

”ተጠቃሚው ለገዛው ንብረትና ምርት ደረሰኝ የመጠየቅ መብቱ የማጠቀም ነዋሪ ቁጥር ቀላል አይደለም።አሰራሩን አጥብቆ ቢይዝ ኑሮ ችግሩን መቀነስ ይቻል እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ እየተባበሳ ያለውን የገበያ የዋጋ ንረት መቀነሰ እንዲቻልም ከፍተኛ ሚና ላላቸው ከ85ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነጋዴዎች ህግና ስርዓት ተከትለው እንዲሰሩ የጋራ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም ”የባሰ ችግር ታይቶባቿዋል የተባሉ ከ12ሺህ በላይ ነጋዴዎች ደግሞ የንግድ ድርጅቶቻቸው እንዲታሸግ ተደርጓል” ብለዋል።

ከጥፋታቸው እንዲታረሙ ተመክረው ያልታረሙ 137 ነጋዴዎች በገንዘብና በእስር እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቋል።

የተገልጋዩ ህዝብ ፍላጎት መሰረት ያደረገ አቅርቦት እንዲኖር በክልሉ የሚገኙ 125 የሸማቾች እና 692 ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበራት በብዛትና ጥራት ምርት እንዲያቀርቡ ከክልሉ መንግስት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ በትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የህብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን አብረሃ ናቸው ።

የትግራይ ህብረት ስራ ማህበራት ከአቅማቸው በላይ የሆነውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታትም ከኦሮሚያ ዩኔን ጋር በጋራ ለመስራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢዜአ

Report Page