#ETH

#ETH


ትናንት ከረፋድ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ጎሃ ፂዮን አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ ተሽከርካሪዎች ማለፍ እንዳልቻሉና ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር መገደዳቸው ተሰምቷል።

ይሄው መንገድ ትናንት ይከፈታል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ዛሬም አለመከፈቱን ተሳፋሪዎችና የደጀን ወረዳ አስተዳዳርና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ካሳሁን አስፋው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ከጎንደር የተሳፈረችው ትዕግስት ደሴ ትናንት ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢው ላይ ሲደርሱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎች ተደርድረው እንደተመለከተችና መንገድ መዘጋቱን እንደሰማች ትገልጻለች።

ተሳፋሪዎቹ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች እንደሆኑ የምትናገረው ትዕግስት፤ ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር እንደተገደዱ ትናገራለች። ደጀን ከተማ ተመላሽ ተሳፋሪዎችን በሙሉ የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ባለመኖራቸው አብዛኛው ሰው በቤተክርስቲያንና ሌሎች ቦታዎች ደጅ ላይ ተጠልለው በከተማው ሕዝብ ምግብና አንዳንድ እርዳታዎች ተደርጎላቸው እንዳደሩ ተመልክታለች።

ዛሬ ጠዋት መንገዱ ይከፈት ይሆናል በሚል ተስፋ ደጀን ያደሩት ተሳፋሪዎቹ፤ መንገዱ ዛሬም ባለመከፈቱ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አረጋዊያን ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ብላለች።

ዛሬ እንደውም ይባስ ብሎ ከአዲስ አበባ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎችም መንገዱ በመዘጋቱ ወደ መጡበት ለመመለስም የትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩን አክላለች። ትናንት ከአዲስ አበባ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች ማለፍ የሚችሉ ቢሆንም ይከፈታል በሚል ተስፋ ግን ከመመለስ ይልቅ መጠባበቁን እንደመረጡ በመናገር።

"የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምዝገባ በጥቅምት አንድና ሁለት ነው፤ እኔ የተሳፈርኩበት አውቶብስ ውስጥ አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ለምዝገባ ለመድረስ የተሳፈሩ ተማሪዎች ናቸው" ትላለች።

ትናንት በነበረው ሁኔታ የሕዝብ ማመላለሻዎች ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ዓይነት መኪና ማለፍ እንዳማይችልም እንደታዘበችም ነግራናለች።

የደጀን ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ኃላፊ የሆኑት አቶ ካሳ አስፋውም በአሁኑ ሰዓት ኦሮሚያ ክልል ያለው መንገድ ስላልተከፈተ ደጀን ከተማ ላይ በርካታ መኪኖችና መንገደኞች በከተማዋ እንዳሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

መንገዱ የተዘጋው ኦሮሚያ ክልል የአባይ በረሃ አፋፍን ወጣ እንዳሉ ወረ ጃርሶ ወረዳ ላይ መሆኑን መስማታቸውን የሚናገሩት አቶ ካሳ ስለምክንያቱ የምናውቀው የለም ብለዋል።

ከትናንት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ በደጀን ከተማ ያለፉ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች መመለሳቸውን የሚናገሩት ኃላፊው ትናንት ቀኑን ሙሉ ከኦሮሚያ ፖሊስ ባልደረቦች ጋር ሲደዋወሉ እንደነበር እና እናጣራለን እንዳሏቸውም ያስታውሳሉ።

ትናንት ከቀኑ አስር ሰዓት ላይ መንገዱ ተከፈተ ተብሎ እንደነበር በመግለፅም መኪኖች መንቀሳቀስ ቢጀምሩም ምሽት አንድ ሰዓት ላይ ማለፍ ባለመቻላቸው በድጋሚ መመለሳቸውን ይገልፃሉ።

መኪኖቹን የፀጥታ ኃይሎች ፈትሸው ቢያሳልፉም ወጣቶች እንደመለሷቸው ከመንገደኞቹ መስማታቸውን ይናገራሉ።

በአንድ ቀን ሰባ፣ ሰማኒያ መኪና፣ በምሽት ደግሞ ከእጥፍ በላይ ከደጀን ወደ አዲስ አበባ መስመር የሚንቀሳቀሱ መኪኖች መኖራቸውን በመናገር ከተማዋ ላይ አሁን ከፍተኛ የመኪና ቁጥር መኖሩን ገልፀውልናል።

በትናንትናው ዕለት በከተማዋ ከ200 በላይ መኪኖች ማደራቸውን ተናግረው፤ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ አዛውንቶች፣ ነፍሰጡሮች እንዳሉ፤ ተማሪዎቹም የመመዝገቢያ ቀን እንዳያልፍባቸው ስጋት እንደገባቸው ያስረዳሉ።

ከትናንት ጀምሮ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች ማለፍ እንደማይችሉ ሌሎች ግን ማለፍ እንዳልተከለከሉ አክለዋል- አቶ ካሳ።

ዛሬ ማለዳ ግን ከኦሮሚያ ፖሊስ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ኃላፊ አቶ ለማ ሆርዶፋ በበኩላቸው ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ የተዘጋበትን ምክንያት ለማጣራት አመራሮችን ወደ ሥፍራው እንደላኩ ገልፀው፤ ዛሬ ጠዋትም በጉዳዩ ላይ ተነጋግረውበት አንድም መኪና መቆም እንደማይችል አቅጣጫ አስቀምጠን መኪና በሰላማዊ መልኩ እያለፈ እንደሆነ መረጃ እንዳላቸው ነግረውናል።

ለእርሳቸው ከመደወላችን በፊት ያነጋገርናቸው ተሳፋሪዎች አሁንም መንገዱ እንደተዘጋ እንደነገሩን ያነሳንላቸው ኃላፊው፤ "በአሁኑ ሰዓት ራሱ መኪና እያለፈ ነው፤ መንገድ ላይ ምንም ችግር እንደሌለ ተጨባጭ መረጃ አለኝ " ብለዋል።

በየትኛውም አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ መኪና በሠላም እየተንቀሳቀሰ እንዳለም አስረግጠዋል።

ትናንት ጠዋት ላይ መንገድ መዘጋቱን ያስታወሱት ኃላፊው "ከምስራቅ ጎጃም ዞን የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረን፤ ወዲያውኑ አቅጣጫ አስቀምጠን ችግሩ ተፈቷል" ብለዋል።

ኃላፊው የሚያጣሩ ሁለት አመራሮችን ወደ ጎሃ ፅዮን መላካቸውን ከመግለፅ ባለፈ እስካሁን ምክንያቱ ተጣርቶ፤ በማንና ለምን እንደተዘጋ ግልፅ መረጃ እንደሌላቸው ነግረውናል።

መንገዱ ስለመዘጋቱ የፀጥታ ኃይሉ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም መባሉን ያነሳንላቸው ኃላፊ"ይህንን ኃላፊነት ወስጄ አጣራለሁ፤ ችግር የለውም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

ከአማራ ክልል የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር አጎራባች አካባቢዎችን በተመለከተ አዳማ ስብሰባ ላይ እንደሚገኙ የገለፁልን ኃላፊው አክለውም፤ በደብረ ብርሃን በኩልም ወደ አዲስ አበባ የሚያስገባው መንገድ ተዘግቷል መባሉንም "ውሸት ነው" በማለት ሰላም መሆኑን እንደሚያውቁ ገልፀውልናል።

BBC

Report Page