#ETH

#ETH


ባለፈው ሳምንት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተለይ ጭልጋ አካባቢ በቅማንት የማንነት ጥያቄ አስመላሽ ኮሚቴና በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ተፈጠረ በተባለው ግጭት በዞኑ ማህበራዊ አገልግሎቶችና መንገዶች እስከመዘጋት መድረሳቸው ይታወሳል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሃብታሙ ጌታሁን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግጭቱ ከተነሳባቸው አካባቢዎች መካከል ቢያንስ በሶስት ወረዳዎች እስከ አሁን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ቆመዋል።

አቶ ሃብታሙ እንደሚሉት "በዞኑ ከሶስት ወረዳዎች ውጭ ሁሉም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየተከናወነ ይገኛል"።

እንቅስቃሴው የተገደበባቸው ሶስቱ ወረዳዎችም ጭልጋ ነባሩ፤ ጭልጋ አዲሱ (በቅማንት የራስ አስተዳደር የተካለለው) እና አይከል ከተማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቀነስ በፍጥነት መሰራቱን የገለጹት አቶ ሃብታሙ የትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተ ከጎንደር መተማ በደርሶ መልስ በቀን ሁለት ጊዜ ጉዞ መኖሩን ገልፀዋል።

"ተሽከርካሪዎቹ በመከላከያ ታጅበው የሚመላለሱ ሲሆን ጥዋት ከጎንደር-መተማ ይሄዱና ማታ ከመተማ ወደ ጎንደር ይመለሳሉ" ብለዋል።

በሶስቱ ወረዳዎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የቆመ ሲሆን፤ እንደገና ያልተጀመረበት ምክንያት "አንደኛ ችግሩ በዘላቂነት ባለመፈታቱና በሌላ በኩል ደግሞ ባለሃብቶቹ 'ንብረቴ ይወድምብኛል' ከሚል ስጋት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ነው" ብለዋል አቶ ሃብታሙ።

ማዕከላዊ ጎንደር የሚገኙት ማለትም ከትክል ድንጋይ ወደ ታች አርማጭሆና ጠገዴ የሚወስዱት ሌሎች የዞኑ መንገዶች ግን ያለምንም የመከላከያ እጀባ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በተያያዘ ሁኔታ ከጭልጋ ወደ ጎንደር የሚጓዙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመታገታቸው ዜና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ተሰራጭቶ እንደነበረ ይታወሳል። አቶ ሃብታሙ ግን ይህ መረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ያስረዳሉ።

"ተማሪዎች ታግተዋል የሚባለው መረጃ እውነትነት የለውም። እንዲያውም ተማሪዎች ወደተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ መጉላላት ሳይደርስባቸው እንዲሄዱ ጥረትና ድጋፍ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

በሶስቱ ወረዳዎች አሁንም በነዋሪው ዘንድ ውጥረትና ስጋት እንዳለ የሚናገሩት ኃላፊው "እንደ አጠቃላይ ግን በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች ምንም አይነት ትንኮሳና ግጭት የለም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በተነሳው ግጭት የሰዎች ህይዎት ማለፉ ቢነገርም የሟቾችን ቁጥርና የወደመውን የንብረት መጠን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ የተናገሩት አቶ ሃብታሙ፤ በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ምርመራ የጀመረው የጸጥታ መዋቅር እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።

BBC

Report Page