#ETH

#ETH


ነባር አባላቱን ባገለለውና ህገወጥ በሆነው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ስም ጥፋት ቢፈፀም ተጠያቂ እንደማይሆኑ የፓርቲው የማዕከላዊ ምክር ቤት የቀድሞ አባላትና አመራሮች አስታወቁ።

የፓርቲው ፕሬዚዳነት አቶ ሰለሞን ታፈሰ በበኩላቸው ቅሬታው ለፓርቲው ህልውና የማይቆረቆሩ አባላት ስሜን ለማጥፋት ያደረጉት ነው ብለዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ /አትፓ/ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አስፋው ጌታቸው በ2007 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ካቀኑ በኋላ በፓርቲው ውስጥ ሁለት ቡድን ተፈጥሮ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል።

በአሁኑ ወቅት አቶ ሰለሞን ታፈሰ ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት እያንቀሳቀሱ ሲሆን የቀድሞው ጠቅላላ ጉባኤ አባላትና በአመራር ላይ የነበሩ አባላት ግን ፓርቲው ህጋዊ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

ለዚህም የፓርቲው ማዕከላዊ ምክር ቤት ታህሳስ 7 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ አቶ አስፋው ጌታቸው ከአሜሪካ እንደተሳተፉበት በቃለ ጉባኤው ላይ የተያዘው መረጃ ያሳያል።

ቃለ ጉባኤው አሁን ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ካሉት ከአቶ ሰለሞን ታፈሰና ሌሎች አምስት አባላት በቀር ሁሉም አባላት መሳተፋቸውን፤ ከስብሰባው አጀንዳዎች መካከልም “በፓርቲው ህልውና ላይ ያነጣጠሩ ችግሮችን ነቅሶ ማውጣትና ውሳኔ ማሳለፍ አንደኛው እንደነበረ መዝግቧል።

ማዕከላዊ ምክር ቤቱ በስብሰባው መጨረሻ አቶ ሰለሞን ታፈሰን ከፕሬዚዳንትነት አግዶ በአቶ አስፋው ጌታቸው ምትክ አቶ መገርሳ ብሩን መምረጡንና ሌሎች የአመራር ሽግሽግ ውሳኔዎችን ማሳለፉም በቃለ ጉባኤው ተገለጿል።

ይሁን እንጂ “ውሳኔው ተቀባይነት ባለማግኘቱ አሁን ያለው አትፓ የቀድሞ አባላትንና አመራሮችን ያገለለ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።

ድርጊቱ ህጋዊ አለመሆኑንና መታረም እንዳለበት የማዕከላዊ ምክር ቤቱ አባላትና አመራሮች በተለያየ ጊዜ ለምርጫ ቦርድ ክስ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።

ይህ ቅሬታ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሲደርስ በቅድሚያ ክስ ለቀረበባቸው ለፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ “ስንት አባላት አሏችሁ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

እርሳቸውም “ያሉንን አባላት አናውቃቸውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ አቶ ሰለሞን ታፈሰ በ2007 ዓ.ም ፓርቲውን ጥለው አሜሪካ ከሄዱት አቶ አስፋው ጌታቸው ቁልፍ ተቀብለው ነባር አባላትን በትነዋል ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።


የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ግን ቅሬታው ለፓርቲው የማይቆረቆሩና የማይሰሩ አካላት ሆነ ብለው ያቀረቡብኝና ስም ለማጥፋት የተደረገ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ አቶ ሰለሞን ታፈሰ ቁለፍ ይዘው ስለሚጠፉ ጠቅላላ ጉባኤ አድርገን አናውቅም፣ ለምርጫ ቦርድም በተደጋጋሚ አቤቱታ አቅርበን መልስ አላገኘንም የሚሉት ደግሞ አቶ መገርሳ ብሩ ናቸው።

አቶ ሰለሞን በነባር አባላት ሳይመረጡ በራሳቸው ሰዎችን ሰብስበው በመሰረቱት ፓርቲና በእጃቸው ባለው ማህተም ጥፋት ቢሰራ ከህግ ተጠያቂነት ማምለጥ አንችልም ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም ነው ያሉት።

“በ2008 ዓም ምልዓተ ጉባኤ አልተሟላም ተብዬ ምርጫው ውድቅ ሆነ ከዚያም በ2010 ምልዓተ ጉባኤውን አሟልቼ ተመረጥኩ” የሚሉት አቶ ሰለሞን በ2010 በተደረገው ምርጫ ብዙዎቹ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት አዳዲስ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ያም ሆኖ አንድም በደብዳቤ የተባረረ አባል የለም የሚሉት አቶ ሰለሞን የተመረጥኩት ሳልፈልግ ነው መምራት ከቻሉ በሩ ክፍት ነው በማለት በምሬት ምላሽ ሰጥተዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም ‘የዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ፓርቲዎች ብዙ ስለሆኑ አጣርተን እንገልጻለን’ ከማለት ውጭ ሌላ ምላሽ አልተገኘም።

ENA

Report Page