#ETH

#ETH


ከታሪክ እንማር

አንድሪዉ ባለበት ቦታ ሁሉ ካሊክስት ከጎኑ አይጠፋም፡፡ በአንድ የቡና ማሳ ዉስጥ አብረዉ እያወሩ ሲሰሩ ይዉላሉ፡፡ የሚዝናንቱም ከቤተሰቦቻቸዉ፣ከሚስቶቻቸዉና ከልጆቻቸዉ ጋር በጊታር በታጀበ ሙዚቃ አብረዉ እየተመገቡ ነዉ፡፡ በቤተ ክርስትያን ዉስጥም ካሊክስት ወንጌል ሲያነብ አንድሪዉ ይሰብካል፤ልጆቻቸዉም በደስታ ይዘምራሉ፡፡ 

በእነዚህ አብሮአደጎች መሀል ንፋስ እንኳን ይገባል ብሎ መገመት ከባድ ነዉ፡፡ ነገር ግን ጥልቅ የሆነ ጥላቻ ለያያቸዉ፡፡ እ.ኤ.አ በሚየዚያ ወር 1994 በተቀሰቀሰ ግጭት ጎረቤት በጎረቤት ላይ፣ ቤተሰብ በቤተሰብ ላይ ተነሳ፡፡ ፍቅር በጥላቻ ተተካ፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት ጓደኛሞችንም ወደ ጠላትነት ቀየራቸዉ፡፡

ይህ እዉነተኛ ታሪክ ከ25 ዓመታት በፊት ከሀገራችን ኢትዮጵያ በ1000ኪሜ ርቀት በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘዉ ሩዋንዳ የተከሰተ ነዉ፡፡

‹‹ሰዎችን መርዳት ስለምወድ ዶክተር ነበር መሆን ምፈልገዉ›› ይላል የሀምሳ አመቱ አንድሪዉ በጽዱ ቤቱ ዉስጥ ቁጭ ብሎ፡፡ ነገር ግን ድህነት ሌላ እቅድ አዘጋጅቶለታል፡፡ ለትምህርት የሚከፍለዉ ገንዘብ ስላልነበረዉ ከ1985 ጀምሮ በወላጆቹ መኖሪያ አካባቢ የራሱን ቤት ሰርቶ መኖር ጀመረ፡፡ ከሁለት አመታት በኋላ ማድሪንን አግብቶ ቤተሰብ መሰረተ፡፡ ‹‹በወቅቱ ጥሩ ህይወት ነበረኝ፡፡ ብዙ ዘመዶችና እንደ አንድ ቤተሰብ የምንተያይ ብዙ ጓደኞች እንዲሁም ጎረቤቶች ነበሩኝ፡፡ ነገሮች ሁሉ እጅግ በጣም ጥሩ ነበሩ፡፡›› አንድሪዉ ያንን ጊዜ በዚህ መልኩ ነበር የሚገልፀዉ፡፡ 

ካሊክስት ደግሞ አሁን 42 አመቱ ነዉ፡፡ ‹‹ያኔ በጣም ንቁ ልጅ ነበር›› ይላል አንድሪዉ ካሊክስትን ሲያስታዉስ፡፡ ‹‹ትምህርት ላይ ደግሞ ጎበዝ ነዉ፡፡ በግጥምና በመዘፈን ደግሞ አንደኛ ነበር፡፡››

ካሊክስት ቀና ብሎ አንድሪዉን እያየ ‹‹በእድሜ ከእኔ ይበልጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ህፃናቶች የምንወደዉን ነገር ነበር የሚሸጥልን፡፡ ብስኩትና ለዉዝ ይሸጥ ነበር፡፡ ሁሌም እነዚህን ለመግዛት ወደሱ እመጣለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ሰዉ ነበር፡፡››

ሁልጊዜ በመንደራቸዉ ሰላምና አንድነት ነበር፡፡ በሰርግም በበዓላትም የመንደሩ ሰዎች በሙሉ ተሰባስበዉ በአንድ ላይ ነበር የሚያከብሩት ፤ እስከ ሚያዚያ 1994 ድረስ፡፡

‹‹ድንገት ነገሮች ተቀየሩ ፤ ሰዎች እርስበርስ መገዳደል ጀመሩ፡፡›› ይላል አንድሪዉ፡፡ ጎረቤቶች በአንድሪዉ ቤተሰብ ላይ ተቀየሩ፡፡ ሚስቱ ማድሪን ከቱትሲ ጎሳ ነች፡፡ አንድሪዉ ሚስቱን እና የሚስቱን ዘመዶች ለማዳን ሞከረ፡፡ ‹‹ለመደበቅ የተቻላቸዉን ሁሉ አድርገዉ ነበር፡፡ አንድአንዶች ቤቴ ድረስ መጥተዉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከተደበቁበት ተገኙና ተገደሉ፡፡›› ማድሪን ብትተርፍም አባትና እናቷን እንዲሁም አምስት ልጆቿን ግን ማትረፍ አልተቻለችም፡፡ ከገዳዮች መሀል ደግሞ ከልጅነቱ ጀምሮ በጣም ይወደዉ የነበረዉ ካሊክስት ይገኝበታል፡፡

እንደ ፓስተር አንትዋን ገለፃ ለዘር ማጥፋቱ ምክንያት በቱትሲና በሁቱ ጎሳዎች መካከል ለአርባ አመታት የነበረዉ መጥፎ ፖለቲካ እና የብሔር እኩልነት አለመኖር ነዉ፡፡ የጥላቻዉን መድረክ ያዘጋጁት ደግሞ ሀገሪቱን በቅኝ ግዛት የወረሩት የአዉሮፓ ሀገራት ናቸዉ፡፡ መጀመሪያ ጀርመን በ1894 በመቀጠል ቤልጀም በ1916 ከጀርመን ተቀበለች፡፡ ከዛም ቤልጀም በ1930ዎቹ የሀገሪቱን ዜጎች በጎሳ ሁቱ፣ቱትሲ እና ትዋ በማለት በመከፋፈል የመታዎቂያ ካርድን ለመጀመሪያ ጊዜ አስተዋወቀች፡፡ ከዛ በፊት ግን ሁሉም ራሳቸዉን የሚያዩት እንደ ሩዋንዳዊ ነበር፡፡

ምንም እንኳን ሁቱዎች የቁጥር ብልጫ ቢኖራቸዉም ቤልጀሞች ግን ቱትሲዎች አላቸዉ ብለዉ በሚያስቡት አካላዊ ልዩነት እንደተሻሉ ጎሳዎች በማየት ለቱትሲዎች ያደሉ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረዉን የዘር መለየት ስራ ከባድ ያደረገዉ ነገር ደግሞ በጎሳዎች መሀል የነበረዉ የእርስበርስ ጋብቻ ነዉ፡፡ አካሄዱን ለማቅለል የአንድ ልጅ ጎሳ ይወሰን የነበረዉ በአባቱ ጎሳ ነዉ፡፡ አንድ ሰዉ ጎሳዉን ካላወቀ ደግሞ ባለዉ የከብት ብዛት ይመደባል፡፡ ከ10 ከብት በላይ ካለዉ የቱትሲ ጎሳ አባል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

ንጉስ ሙራታ በ1959 እስኪሞት ድረስ የቱትሲ ነገስታት ሩዋንዳን ሲያስተዳድሩ ነበር፡፡ በዛ ዓመት ግን ጭሰኛ ገበሬዎች የሁቱ አመፅ ‹‹HUTU REVOLUTION›› በመባል የሚታወቀዉን እንቅስቃሴ በመጀመር ዘዉዳዊዉን አገዛዝ ለመጣል በቁ፡፡ በወቅቱም የነበረዉ የእርስ በርስ ጦርነት የአንቱዋንን አባት ጨምሮ የ 150 000 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ብዙ ቱትሲዎችም ወደ ብሩንዲና ሌሎች የጎረቤት ሀገሮች ተሰደዱ፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ ግማሽ የሚሆኑት የቱትሲ ጎሳዎች የሚኖሩት ከሩዋንዳ ዉጭ ነበር፡፡

የሁቱ ጎሳ ስልጣን ከያዘ በኋላ መንግስት ፅንፈኛ የሆኑ ሰዎችን በመጠቀም በቱትሲዎች ላይ የሬድዮ የጥላቻ መልክቶችን ማስተላለፍ ጀመረ፡፡ በረሮዎች እያለ የሚጠራቸዉን የቱትሲ ጎሳዎች እንዲያጠቁና እንዲገድሉም የሁቱ ጎሳዎችን መቀስቀስ ጀመረ፡፡

ለአንትዋን ቱትሲ መሆኑ በየጊዜዉ አደጋ ላይ የሚጥለዉ ጉዳይ ነበር፡፡ ‹‹በየአስር አመቱ በምጠላበትና እንደ ሁለተኛ ዜጋ በምቆጠርበት ሀገር ዉስጥ መኖሬን የሚያስታዉሰኝ ነገር አለ፡፡›› ይላል አንትዋን፡፡ በ15 አመቱ ከት/ቤት ተባረረ፤ በ25 አመቱ ከስራ ተባረረ፤ በ35 አመቱ ማለትም በ1994 ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆነ፡፡

በ1994 ሚያዚያ 6 ቀን ምሽት ላይ የሁቱ ጎሳ ተወላጅ እና የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት የነበረዉን ጁቪናል ሀቢያሪማናን ይዞ ይሄድ የነበረ አዉሮፕላን በተተኮሰ ሚሳኤል ተመትቶ ኪጋሊ አየር ማረፊያ አካባቢ ወደቀ፡፡ ፕሬዝዳንቱና ዉስጥ የነበሩት ሰዎችም ሞቱ፡፡ ይህ ክስተት አለማችን ላየችዉ እጅግ አስከፊ የዘር ጭፍጨፋ መነሻ ምክንያት ሆነ፡፡ በቀጠሉት 100 ቀናት ዉስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት የሩዋንዳ ህዝቦች በሚያሰቅቅ ሁኔታ ተገደሉ፡፡ ይህ ክስተት ሰላምን፣ ጓደኝነትን፣ ቤተሰብን ብሎም ማህበረሰብን በታተነ፡፡

የብዙ ሰዎች ህይወት ካለፈበት ቦታ መካከል አንዱ ደግሞ አንድሪዉ የሚኖርበት መንደር ነዉ፡፡ በስምንት ሰአታት ዉስጥ ብቻ በመንደሩ በሚገኝ የትምህርት ቤት ዉስጥ ተጠልለዉ የነበሩ 50 000 ቱትሲዎች ተጨፈጨፉ፡፡

በመጨረሻም የአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሚ የሚመሩት የቱትሲ ጎሳ አባላትንና ለዘብተኛ የሚባሉ ሁቱዎችን የያዘዉ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ጦርነቱ ከተጀመረ ከ100 ቀናት በኋላ ነሀሴ 4 ቀን 1994 ዋና ከተማዋ ኪጋሊ ገቡ፡፡ ጦርነቱም ተፈፀመ፡፡ በ100 ቀናት ዉስጥ ግን 800 000 ሰዎች ተገደሉ፡፡

ይህን ቁጥር ለማነፃፀር ይረዳን ዘንድ ከመዲናችን አዲስ አበባ ቀጥሎ ብዙ ህዝብ የሚኖርባቸዉን የሀገራችን ከተሞችና የህዝብ በዛት

ጎንደር 

መቐለ

አዳማ

ሀዋሳ

ባህር ዳር

ይህ ማለት የሀገራችን ሁለት ትልልቅ ከተሞች ባዶ በሆኑ እንኳን የማንደርስበት ቁጥር ነዉ፡፡ እነሱ በገጀራ 800 000 ድረስ ከተጨራረሱ እኛ በጠመንጃ የት ልናደርሰዉ እንደምንችል መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ይህን ነገር ካሁኑ መላ እንበለዉ እላለሁ፡፡  

                                               

ኅሩይ

ከጎንደር ዪኒቨርሲቲ

ቸር ወሬ ያሰማን!

Report Page