#ETH

#ETH


ተጠርጣሪው ለከፈተው ተኩስ በተወሰደ አጸፋ ህይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን የጸጥታ ችግር በመፍጠር ተጠርጥሮ በህግ የሚፈለግ ግለሰብ በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ ከፍቶ በአጸፋ ምላሽ ህይዎቱ ማለፉን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ብርሃኑ ገላው ለአብመድ እንደገለጹት የቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ አባል እንደነበረ የሚታወቀው አስቻለው ደሴ የተባለው ግለሰብ 31 አባላትን በማደራጀት በዞኑ በሚገኙ ከተሞች በመንቀሳቀስ፣ መኪና በማስቆም እና ንብረት በመዝረፍ ተጠርጥሮ በህግ ሲፈለግ ነበር፡፡ ግለሰቡ በነፋስ መውጫ፣ በወረታ፣ በአዲስ ዘመን፣ በሊቦ ከምከም፣ በእብናት እና በሌሎች ወረዳዎች እየተንቀሳቀሰ ሰዎችን በማስፈራራት ንብረት ይዘርፍ ነበር በሚል ተጠርጥሮ እንደነበረም ነው ኮማንደር ብርሃኑ የተናገሩት፡፡

ከዚህ ባለፈም የአንድ የፖሊስ አባል ህይዎት በማጥፋት ተጠርጥሮ ሲፈለግ ነበር ብለዋል ኮማንደር ብርሃኑ፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበትና የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቶበት በማረሚያ ቤት የቆዬ ቢሆንም በሀገራዊ ይቅርታ ተጠቃሚ በመሆን ከእስር ቤት ወጥቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ህገ ወጥ ተግባሩን መቀጠሉን እና በክልሉ ሰኔ 15 ላይ በተፈፀመው የከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የፖሊስ አባላት ግድያ ተጠርጥሮ በህግ ሲፈለግ መቆቱንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ይገኝበታል በተባለው እብናት ወረዳ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋልና ህግን ለማስከበር የጸጥታ አካላት፣ የሀይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ሽማግሌዎች ለህግ እጁን እንዲሰጥ ቢጠይቁትም ፈቃደኛ ካለመሆኑ ባለፈ በግለሰብ እጅ ሊያዝ በማይገባው ብሬል የተሰኘ የጦር መሳሪያ ወደ ጸጥታ አካላት ተኩስ መክፈቱን ኮማንደሩ ገልጸዋል፡፡

በተወሰደ የአጸፋ እርምጃ የግለሰቡ ህይወት ማለፉንም ኮማንደር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የሚያውኩ አካላትን በመከላከል ሥራው ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

AAMA

Report Page