#ETH

#ETH


በድሬዳዋ ቀፊራና አካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን እንዲያረጋግጥ ባካሄዱት ሰልፍ ጠየቁ።

በድሬዳዋ ቀፊራ፣ አምስተኛ፣ ገንደጋራ፣ ቀብረ ጆሌና ሌሎች አካባቢዎች የተወጣጡ ሴቶችና ወጣቶች ዛሬ ባደሩት የአደባባይ ሰልፍ ላይ እንዳሉት በሚኖሩበት አካባቢ የተደራጁ አካላት ሰርተው በሰላም እንዳይኖሩ እያደረጓቸው ነው።

ሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት “ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል፣ በሰላም እጦት ልጆቻችንን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አልቻልንም” ብለዋል።

የሰልፈኞቹ ተወካዮችም ሰልፉን ተከትሎ ከአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ተወካዮቹ በእዚህ ጊዜ በድሬዳዋ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፍቅርና አንድነትን የማይፈልጉና የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ያነገቡ የተደራጁ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ይህን የጋራ እሴት እየሸረሸሩና እያፈረሱት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለዘመናት ለፍተው ያፈሩት ሀብትና ንብረት እየተዘረፈባቸው መሆኑን ነው ያስታወቁት።

መንግስት አስተማማኝ ሰላም በማስፈን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና ሁሉም በሰላም እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት እንዲወጣም ተወካዮቹ ጠይቀዋል።

ውይይቱን የመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሀር የአስተዳደሩን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በድሬዳዋ የህዝቡን ሰላምና ጸጥታ እያወኩ ያሉ ወንጀለኞች ለህግ እንደሚቀርቡም አረጋግጠዋል።

ነዋሪው እርስ በርስ እንዲጋጭ በተለያዩ ጊዜያት ከሚነሱ አሉባልታዎች በመራቅ ለዘመናት ያዳበረውን አንድነትና መተሳሰብ ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

ዛሬ ከ10፡00 ሰዓት ጀምሮ ችግር በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል ።

Via #ENA

Report Page