#ETH

#ETH


ግብጽ በሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ላይ ያነሳችው አቋም የኢትዮጵያን ቀይ መስመር የሚያልፍ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ዙሪያ ያነሳችው አቋም የኢትዮጵያን ቀይ መስመር የሚያልፍ በመሆኑ መግባባት ላይ አለመደረሱን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበርያ ምክር ቤት ጽሐፈት ቤት በግድቡ ሁለንተናዊ ጉዳይ ዙሪያ ከተለያዩ አካላት ጋር ዛሬ ምክክር አካሂዷል።

በመድረኩ የግድቡ ግንባታ ያለበትን ደራጃ እና የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሦስትዮሽ ውይይት ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ሐሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎበታል።

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ አማካሪ አቶ ተፈራ በየነ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል እየተደረገ ባለው የሦስትዮሽ ውይይት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ግብጽ ‹‹በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውኃ ይለቀቅልኝ›› ማለቷ እና ‹‹የአስዋን ግድብ ከፍታ ከባሕር ጠለል በላይ 165 ሜትር ሲደርስ ኢትዮጵያ ውኃ መልቀቅ አለባት፤ እንዲሁም ሦስተኛ ወገን በአደራዳሪነት ይግባ›› የሚል አቋም ማቅረቧን አንስተዋል።

ፋብኮ እንደዘገበው ግብጽ በውይይቶቹ ላይ እያነሳች ያለው አቋም በኢትዮጵያ በኩል የኅልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ውድቅ መደረጉን ነው አቶ ተፈራ የገለጹት።

ግብጽ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ የምታነሳቸው ሐሳቦች የኢትዮጵያን ቀይ መስመር የሚያልፉ መሆኑንም አቶ ተፈራ አንስተዋል።

ግብጽ በካርቱም በተደረገው ስብሰባ ላይም ብዙ የማያግባቡ አጀንዳዎችን ስታቀርብ እንደነበርና በውይይቶቹ ላይ እያሳዬች በሚገኘው አቋም ደግሞ ከመግባባት ላይ መድረስ እየተቻለ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በካርቱሙ ውይይት ላይ ሦስቱም ሀገራት በተናጠል ካቀረቧቸው ሐሳቦች መካከል ውስጥ ኢትዮጵያ ‹‹ግድቡ በሦስት ደረጃ ውኃ ይሞላ›› በሚል እና ‹‹ሁለቱ ተርባይኖች ያለ ቅድመ ሁኔታ ሥራ ይጀመሩ›› የሚለው ላይ መስማማት ላይ ቢደረስም ግብጽ ‹‹እኔ ያቀረብኩት ሐሳብ ሙሉ ተቀባይነት ካላገኘ በእነዚህ ላይ ቃለ ጉባዔ አይያዝም›› ማለቷንም አስታውቀዋል።

ግብጽ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውኃ አሞላል ላይ የምታቀርባቸው ሐሳቦችን መቀበል ማለት ያሁኑን ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ የኢትዮጵያ ትውልድ ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የግድቡ አሞላል ውይይት ከፖለቲካ ወጥቶ ቴክኒካዊ እስከሆነ ድረስ ውይይቱን ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በመድረኩ ላይ የግድቡ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ያነሱ ገልጸዋል፤ የግድቡ ግንባታ በዚህ ወቅት 68 ነጥብ 56 በመቶ ላይ መድረሱን እንዳስታወቁ የፋብኮ ዘገባ ያስረዳል።

ሁለቱ ተርባይኖች ወደ ኃይል ማምረት እንዲገቡ ለማድረግ ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ባለፈው በጀት ዓመት ከቦንድ ሽያጭና መሰል የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች 970 ሚሊዮን ብር ከኅብረተሰቡ መሰብሰቡም ተመላክቷል።

Via #FBC

Report Page