#ETH

#ETH


በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም. የተመረቀው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ለ‹‹ቋሚና ተወርዋሪ ኃይል›› እንጂ መደበኛ ፖሊስን እንደማይመለከት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥቁር ሰማያዊ ኮፍያና ሱሪ በውኃ ሰማያዊ ሸሚዝ የነበረውን የፖሊስ የደንብ ልብስ፣ ጠቆር ባለ ክብ ኮፍያ (ቦኔት) እና ግራጫ ዥንጉርጉር የደንብ ልብስ መቀየሩን በሚመለከት፣ ‹‹ለምን መቀየር አስፈለገ?›› የሚል ጥያቄ በተለይ በከተማው ነዋሪዎች በመነሳቱ ሪፖርተር ኮሚሽኑን አነጋግሮ ምላሽ አግኝቷል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፣ ‹‹የደንብ ልብሱን ለምን መቀየር አስፈለገ?›› ለሚለው ጥያቄ፣ ‹‹ነባሩ የፖሊስ የደንብ ልብስ አልተቀየረም፡፡ ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ በተጨማሪነት ሊሰጥ ይችላል፡፡ አዲሱ የደንብ ልብስ የተዘጋጀው በሌሎች ክልሎችም እንዳለው ሁሉ፣ ከመደበኛ ፖሊስ በተለየ በከተማው ውስጥ ሁከት ሲፈጠርና ከመደበኛው ፖሊስ አቅም በላይ ሲሆን፣ ያንን ለሚቆጣጠር ቋሚና ተወርዋሪ ኃይል የተዘጋጀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ቋሚና ተወርዋሪ›› ኃይሉ በዋና ዳይሬክተር የሚመራና ሙሉ ትጥቅ ያለው ኃይል ሲሆን፣ ለከተማ አስተዳደሩ ጥበቃ የተዘጋጀ የ‹‹ክብር ዘብ›› መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

የደንብ ልብሱ ለጊዜው መደበኛ ፖሊሱን እንደማይመለከትም ዳይሬክተሩ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ የደንብ ልብሱ የተዘጋጀው በከተማው ድንገተኛ ችግር ቢከሰትና ከአቅም በላይ ከሆነ ተወርውሮ በመድረስ አድማ ለሚበትነው ኃይል መሆኑንም አክለዋል፡፡

በከተማው ውስጥ አድማ በታኝ የፌዴራል ፖሊስ እያለ፣ ተጨማሪ ኃይል ማደራጀት ለምን አስፈለገ? ተብለው የተጠየቁት ዳይሬክተሩ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተባብሮ የሚሠራ ቢሆንም፣ ተጨማሪ ኃይል በማደራጀት ከተማው የራሱ ፖሊስ እንዲኖረውና ከተማዋን የሚመጥን ኃይል እንዲኖር በማስፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የደንብ ልብሱን ከመደበኛ ፖሊስ ጋር ማለያየቱ ለምን እንዳስፈለገም ተጠይቀው፣ መደበኛው የደንብ ልብስ ከጥራት ጋር በተገናኘም በርካታ ችግሮች ስለነበሩበት እሱን ለማስወገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነባሩ የደንብ ልብስ አንድ ጊዜ እንደታጠበ የሚበላሽና ከተማዋንም የሚመጥን ባለመሆኑ፣ ያንን ትችት ለማስቀረት ታስቦ መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የደንብ ልብሱ ለሁሉም መዘጋጀቱን የሚያሳይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ዥንጉርጉር የሆነ ወታደራዊ ልብስ በከተማ ደረጃ ፖሊስ ለብሶት ካለመለመዱም በተጨማሪ፣ ሕዝቡ የደንብ ልብሱን ሲያይ የፍርኃት ስሜት እንዲሰማው ሊያደርግ እንደሚችልና ከሕዝብ ጋር ተባብሮ ወንጀልን ይከላከላል ተብሎ በሚታሰበው የፖሊስ ሥራ ላይ እንቅፋት ስለመፍጠሩ ተጠይቀው፣ ድሮም (በደርግ ጊዜ) ቢሆን የልብሱ መልክ ሌላ እንደነበርና ማዕረጉም ጭምር መቀየሩን ጠቁመው፣ መደበኛ ፖሊስ ቢለብሰውም ችግር እንደማያመጣ ገልጸዋል፡፡

በከተማው ቻርተር መሠረት የፖሊስ የደንብ ልብስ ምን መምሰል እንዳለበት ተደንግጎና በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ መሠረት የደንብ ልብሱ ስለመዘጋጀቱ ተጠይቀው፣ ቻርተሩም ሆነ ደንቡ የተሻሻለበት ሁኔታ እንደሌለና መመርያ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበት በሥራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 96/1996 አንቀጽ 3(2) እና በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 መሠረት ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ ሆኖ የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡

REPORTER

Report Page