#ETH

#ETH


በአጣዬ 8 ሰዎች ተገደሉ ተባለ!

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማና አካባቢዉ ከትናንት በስቲያ በተቀሰቀሰዉ ግጭት የ5 ሰላማዊ ዜጎች እና ሕይወት ማለፉ ተገለፀ። በግጭቱ ከመንግሥት ወገን 3 የፀጥታ ኃይላት መሞታቸውንና 5 መቁሰላቸውም ተገልጧል።

የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌታቸዉ በቀለ እንደገለፁት በአካባቢዉ ግጭቱ የተቀሰቀሰዉ ከ3 ቀን በፊት አንድ የታጠቀ ግለሰብ የክልሉ ልዩ ኃይል በሚገኝበት የጥበቃ ማማ ላይ በከፈተዉ ተኩስ ነዉ።

ግለሰቡ ጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በማይቻልበትና በኮማንድ ፖስት ስር ባለ አካባቢ 3 የእጅ ቦንቦች፤ ክላሽንኮቭ እና በርካታ ጥይቶችን ይዞ በመገኘቱ በተኩስ ልዉዉጥ እንደተገደለ አቶ ጌታቸዉ ዐስታዉቀዋል።

ይህንን ተከትሎ ያለፉት 3 ቀናት በአጣዬ ከተማና በአካባቢዉ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ጭምር በርካታ ቁጥር ያላቸዉና «ያልታወቁ »ያሏቸዉ የታጠቁ ኃይሎች በአካባቢዉ ነዋሪዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸዉን ተናግረዋል። በዚህ ግጭትም በአካባቢዉ ገጠር ቀበሌዎች የአምስት ሰላማዊ ዜጎች ሕይወት መቀጠፉን ከንቲባዉ አብራርተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የመንግስት የኮሚንኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ማሙሽ ይልማ በኩላቸዉ፦ ጥቃቱን ያደረሱት የኦነግ ሰራዊት አባላት መሆናቸዉን ገልፀዉ፤ በግጭቱ ከመንግሥት ወገን 3 መሞታቸውንና 5 መቁሰላቸውን ተናግረዋል፡፡

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ «አጣዬ ኦነግ ምን ሊሰራ ይመጣል፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት እንደሌለው ብዙ ጊዜ መላልሰን ተናግረናል፤ በምንም መልኩ ኦነግ ሰራዊት የለውም። 

ሰራዊት የሌለው ድርጅት ደግሞ ለምን ሰሙ እንደሚጠቀስ አናውቅም፡ አጠቃላይ ስሞታው ውሸት ነው። የኦነግን ስም ለማጠልሸት የሚደረግ ነገር ነው” ሲሉ ለባህርዳሩ ዘጋቢያችን ዓለምነዉ መኮነን ገልጠዋል።

እንደ አቶ ጌታቸዉ በአጣዬና በአካባቢዉ ገጠር ቀበሌዎች አሁንም ድረስ ዉጥረት በመንገሱና ተኩስ በመቀጠሉ ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም።

በአካባቢዉ ዉጥረቱን ለማርገብ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፌደራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን፤ ተጨማሪ ኃይል እንዲገባ እየተጠየቀ መሆኑንም ከንቲባዉ አመልክተዋል።

ይህን መሰሉ ጥቃት ከዚህ ቀደም በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም እና በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ተቀስቅሶ የሰዉ ሕይወት መጥፋቱን፤ በርካታ ንብረት መዉደሙን እንዲሁም ቤተ እመነቶች እና የመንግስት ተቋማትም መቃጠላቸዉን ኃላፊዉ ለዶይቸ ቬለ አክለው ተናግረዋል።

Via ዶቸቪሌ ነው

Report Page