#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ዙሪያ የተጀመረውን የሶስትዮሽ ቴክኒካዊ ምክክር ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነው

============================================

የግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የውሀ ጉዳይ ሚኒስትሮች መስከረም 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም በካይሮ ባካሄዱት ስብሰባ ባስቀመጡት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በካርቱም የሶስትዮሽ ስብሰባቸውን አካሂደዋል፡፡ ከሚኒስትሮቹ ስብሰባ አስቀድሞ የአገራቱ ገለልተኛ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድን ከመስከረም 19 እስከ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በካርቱም አምስተኛ ዙር ስብሰባውን አካሂዶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በአገራቱ መካከል የሚደረገው ቴክኒካዊ ምክክር ብቸኛው የመፍትሄ አማራጭ በመሆኑ መቀጠል እንደሚኖርበት ያምናል፡፡

የሳይንሳዊ ቡድኑ አራት ስብሰባዎችን አድርጎ አበረታች ውጤት እያሳየ ባለበት ወቅት ግብጽ በተናጠል ያቀረበችው የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅን የሚመለከተው ሰነድ ከትብብር ማዕቀፉ ውጪ የሆነ እና ሂደቱን ያናጠበ ሆኗል፡፡ ሆኖም የውሃ ሚኒስትሮች የኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ እቅድ፣ የግብጽ መንግስት የሚያቀርበው ሰነድ እንዲሁም ሱዳን በጉዳዩ ላይ የምታቀርበው ሰነድ ለሳይንሳዊ ቡድኑ ቀርቦ ዝርዝር ትንታኔ እንዲደረግበት እና ምክረ ሃሳብ እንዲቀርብለት በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በካይሮ በተደረገው ስብሰባ ወስነዋል፡፡

በካርቱም አራት ቀናትን ወስዶ በተካሄደው ስብሰባ የሳይንሳዊ ቡድኑ በመስከረም ወሩ የካይሮ ስብሰባ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የኢትዮጵያን የግድብ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ ዕቅድ፣ እንዲሁም ሱዳን እና ግብጽ ያቀረቡትን የሙሌት እና የውሃ አለቃቅ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰውን ሃሳብ አዳምጦ ውይይቶችን አካሂዷል፡፡ ውይይቱ ሶስቱም ቡድኖች በተስማሙበት የርዕሰ ጉዳይ መዘርዝር ላይ የተመሰረተ ሲሆን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመስማማት ተደርሶ በሌሎቹ ላይ የሃሳብ መለያየቶች ተመዝግበዋል፡፡

እነዚህ የሃሳብ ልዩነቶች በሳይንሳዊ እና ጥናት ቡድኑ ውይይት እና ትንተና መግባባት ሊደረስባቸው የሚችሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡን እሰከ ሰባት አመት ድረስ በሚወስድ ሂደት ለመሙላት ያቀረበችው እቅድ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ጥቅም ለመጠበቅ ያላትን አቋም ያሳያል፡፡ ይህም በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ሱዳን ማናቸውም ቱክኒካዊ ጉዳዮች ለሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ቀርበው ትንተና እንዲደረግባቸው ገንቢ እና አካታች የውይይት አካሄድ ቢከተሉም የግብጽ ወገን ያቀረብኳቸው ሃሳቦች በሙሉ ተቀባይነት ካላገኙ ውይይቱ ሊቀጥል አይችልም በሚለው የማያሰራ አቋሙ በመቀጠሉ የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ስራውን በተሟላ አኳኋን ማከናወን ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህ የግብጽ አቋም የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ ስብሰባ እንዲሁም የሚኒስትሮች ስብሰባው ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ጭምር ሪፖርት እንዳያዘጋጁ አድርጓል፡፡

ይህ የግብጽ አካሄድ አዲስ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም በግድቡ ላይ ሶስቱ አገራት ሊያከናውኑት የነበረውን የውሃ፣ የአካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተጽእኖ ጥናት በግብጽ ወገን እንዲስተጓጎል በተደረገ ጊዜ የታየ የሳይንስ እና የምክክር የመፍትሄ አማራጭን የማፋለስ ዘዴ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አለመግባባት መፍቻ ዘዴን የሚደነግገውን የመርህ መግለጫ ስምምነቱን አንቀጽ 10 ጠቅሶ መፍትሄ ለመፈለግ ጊዜው እንዳልሆነ እና ቴክኒካዊ ምክክሩ ሊቀጥል እንደሚገባ ታምናለች፡፡

የውሃ ሚኒስትሮቹ በሁለት ቀናት ስብሰባቸው የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ የደረሰበትን ተመልክተው አቅጣጫ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የግብጽ ወገን ቀድሞውኑ የምክክር ሂደቱ እንዲፋረስ አቋም ይዞ የመጣ በመሆኑ ጉባኤው የሳይንሳዊ ጥናት ቡድኑ በቀጣይነት ማከናወን ስላለበት ተግባር መመሪያ ሳያስተላልፍ ቀርቷል፡፡

የግብጽ መንግስት ሶስተኛ ወገን በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ እያቀረበ ያለው ሃሳብ በሶስቱ አገራት የትብብር መድረክ የታየውን አበረታች ሂደት የሚያጣጥል እና ሶስቱም አገራት በመጋቢት 2007 ዓ.ም. የፈረሙትን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት የሚጥስ ተግባር ነው፡፡ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ-ገብነት ኢትዮጵያ እና ሱዳን የማይቀበሉት እና ተገቢ ያልሆነ፤ በአገራቱ መካከል ያለውን ዘላቂ ትብብር የሚጎዳ፤ ለውይይት ያለውን በቂ እድል ወደጎን የሚያደርግ እና ገንቢ የሆነውን የውይይት መንፈስ የሚያደፈርስ ነው፡፡

ቴክኒካዊ ምክክር የሚጠይቀው የግድብ ሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ጉዳይ ለፖለቲካ ምክክር እንዲቀርብ የሚጠይቀው ሃሳብም የጉዳዩን ጠባይ ያላገናዘበ፣ የሶስቱ አገራት መሪዎች የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉዳዩን ለመፍታት የሰጡትን መመሪያ የጣሰ እንዲሁም ተገቢ መፍትሄ ለመስጠት የማያስችልም ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ልዩነቶችን ለመፍታት እድል የሚፈጥረውን የምክክር ሂደት ለማጠናከር እንደሚሰራ እየገለጸ በጉዳዩ ላይ የሚሰራጨው የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ሌላ አሉታዊ ዘመቻ የሶስቱን አገራት መተማመን ከመሸርሸር ያለፈ ውጤት እንደማይኖረው ይገልጻል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለጸው የአባይን ውሃ የኢትዮጵያ ህዝቦችን የአሁን እና የወደፊት ፍላጎት ለማሟላት እና ብሄራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ማልማቱን በመቀጠል ርትዕን የጠበቀ እና በማናቸውም የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ አጠቃቀም እንዲኖር ይሰራል፡፡

በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት በሕዳሴ ግድብ ላይ በሚደረገው ውይይት የሚከተለው አቅጣጫ የናይል ውሃን አስመልክቶ ለተደረጉት እና በኢትዮጵያ ላይ ምንም አይነት ተፈጻሚነት የሌላቸውን ስምምነቶች እውቅና የማይሰጥ እንዲሁም የላይኛውን የናይል ተፋሰስ አገራት መብት የማይጥስ እንዲሆን ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

Report Page