#ETH

#ETH


በምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ሰባት ሰዎችን አሳፍራ የአዋሽ ወንዝን በመሻገር ላይ የነበረችው ጀልባ ብትገለበጥም ተሳፋሪዎቹ በሙሉ በኢትዮጵያ አየር ሃይል ድጋፍ ከወንዙ በህይወት መውጣታቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ዛሬ እንደገለጹት ጀልባዋ ትናንት ጧቱ 1 ሰዓት ላይ የተገለበጠችው በሉሜ ወረዳ ዱንጉጊ ቀበሌ ገበሬ ማህበር አካባቢ ባለው የአዋሽ ወንዝ ነው ።

ሰባት የአካባቢው አርሶ አደሮች ለእርሻ ስራ ከእንጨት በተሰራችው ጀልባ ወንዙን ለመሻገር በጉዞ ላይ እንዳሉ አደጋው መድረሱን ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

ጀልባዋ የተገለበጠችው በወቅቱ በአካባቢው በነበረው ሃይለኛ ንፋስ ምክንያት ነው ተብሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከተገለበጠችው ጀልባ ወንዝ ውስጥ የገቡትን ሰዎች በዋና ለማውጣት ርብርብ ቢያደርጉም የወንዙ ፍሰት አስቸጋሪ ስለነበር ማውጣት የቻሉት ሁለቱን ብቻ ነበር ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የሁኔታውን አስቸጋሪነት በመግለፅ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ድጋፍ መጠየቁን የገለፁት ኮማንደሩ የአየር ሃይሉ አባላት በፍጥነት በቦታው ደርሰው ቀሪዎቹን በሙሉ በህይወት እንዲወጡ አድርገዋል ።

የአየር ሃይል አባላቱ በውሃውና በአውሎ ንፋስ ተገፍተው እንቦጭ ውስጥ የተዘፈቁትን አርሶ አደሮች ከሔሊኮፕተር በፓራሹት እየወረዱ በህይወት እንዲወጡ በማድረጋቸው ከአካባቢው ህብረተሰብ አድናቆት ተችሮአቸዋል ።

ኮማንደሩ እንዳሉት የኢፌዴሪ አየር ሃይል የህብረተሰቡን የልማት ሥራዎችና የሀገር ሉዓላዊነትን ከማገዝ በተጓዳኝ በአካባቢው የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ዋጋ በመክፈል ጭምር ወገኖቹን በመታደግ ህዝባዊነቱን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል ።

የኢፌዴሪ አየር ሃይል ላደረገው እገዛም የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ በዞኑ ህብረተሰብ ስም ምስጋና አቅርቧል።

Via ኢዜአ

Report Page