#ETH

#ETH


የኢሬቻ በዓልን በተመለከተ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ:-

ከሁሉም በማስቀደም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ወንድም ለሆነው የኦሮሞ ሕዝብ እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልፃል።

የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የኖረ ፣ ክፉ ደጉን በጋራ ያሳለፈ፣ የተጋባ፣ የተዋለደ፣ የተዋሃደ ሕዝብ ነው። ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈጠሩት ጥራዝ ነጠቅና በአማራ ጥላቻ የሰከሩ ብሔርተኞች የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት የጨቋኝና የተጨቋኝ ፤ አለፍ ሲልም የቅኝ ገዢና ተገዢ አድርገው በማቅረብ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ጠንካራ ትስስር ለማላላት ቢሰሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ዛሬም እንደትላንቱ የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በጋራ አርሶ፣ ነግዶ፣ ሰርቶ፣ ተጎራብቶ ፣ እየተጋባና እየተዋለደ፣ በሃዘን በደስታው እየተገናኘ አብሮ እየኖረ ነው::

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ስህተት እንደነበርና በኢትዮጵያ የአማራ ብሔር ጨቋኝነት እንዳልነበረ አንዳንድ የኦሮሞ ፓለቲከኞች በአደባባይ እስከመግለፅ ደርስዋል:: በዚህ አጋጣሚ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እንደዚህ ያለ አቋም እያራምዱ ላሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያለውን አድናቆትና ክብር መግለፅ ይወዳል::

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ካላቸው የዘመናት ትስስርና መዋሃድ የተነሳ የወደፊት እጣ ፈንታቸው በእጅጉ የተሳሰረ ነው ብሎ ያምናል። የሁለቱ ሕዝቦች ጥቅሞችና ህልሞችም የግድ የሚጋጩ ሳይሆኑ በሰለጠነ፣ በሰከነና ስርዓት ባለው ውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ በተቃኘ ድርድር ሁለቱም ሕዝቦች አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል እንዳለ ይገነዘባል።

ከዚህ በተቃራኒ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል በልሂቃን ቆስቋሽነት ሊፈጠር የሚችል ግጭትና አለመግባባት ለአገራችንም ሆነ ለቀጣናው አለመረጋጋት በመፍጠር ሁለቱን ሕዝቦች ሰላም ሊያደፈርስረና ከፍተኛ ጉዳት ሊጋብዝ የሚችል እንደሆነም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይረዳል።

በዚህ አጋጣሚ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ለተራማጅ የኦሮሞ የፓለቲካ ድርጅቶች በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ጥላቻንና ጥርጣሬን ከሚዘሩ አማራ ጠል ኃይሎች እጅ ወጥቶ ወደ ሰለጠነና የሁለቱንም ሕዝቦች ተጠቃሚነት ወደሚያረጋግጥ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን እየገፀ፤ የሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃንና ፖለቲከኞችም የሕዝቦቻችንን ታላቅነት ወደሚመጥን ግንኙነት በማሳደግ ረገድ አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ማሳሰብ ይወዳል::

በድጋሚ መልካም በዓል!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

መስከረም 23 ቀን 2012 ዓ/ም

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ

Report Page