#ETH

#ETH


መስከረም 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ከተሞች የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም

ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ፦

ከሀገራችን አልፎ በዓለም ከማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ ሆኖ በዩኒስኮ የተመዘገበው ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ በርካታ የውጭ ጎብኝዎች የታደሙበት የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ከተማና በመላው ሀገራችን በድምቀትና በሰላም መከበሩ ይታወሳል። ለዚህም በዓል በሰላም መከበር መላው የሀገራችን ህዝቦች ላደረጋችሁት ቀና ትብብርና ድጋፍ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ላቅ ያለ ምስጋናውን ማቅረብ ይወዳል።

እንደ ደመራ በዓል ሁሉ ከዘመን መለወጫ በዓል ጋር ተያይዞ ሌላው በየአመቱ በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ የማይዳሰሱ የሀገራችን ቅርሶች ውስጥ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው የኢሬቻ በዓል አንዱ ነው፡፡ በዚሁ የሀገራችን ባህላዊ የእምነት እሴት መገለጫ በሆነው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ ከኦሮሞ ህዝብ ባሻገር መላው የሃገራችን ህዝቦችና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የሚሳተፉበት ታላቅ በዓል ነው ፡፡

ዘንድሮ በአዲስ አበበ ከተማ መስከረም 24 ቀን እና በቢሾፍቱ ከተማ መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ/ም በድምቀት የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ለማደናቀፍ፣ የተለያዩ አካላት የራሳቸው አጀንዳ ለማስፈፀም እና ለጥፋት ይጠቀሙበት የነበሩ የጦር መሳሪያዎችና ቦንቦችን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለማስገባት ሲሞክሩ ከዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ጋር በህብረተሰቡ ትብብርና በፀጥታ ሀይሉ የተቀናጀ ጥረት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽኑ ማስገንዘብ ይፈልጋል፡፡

በመሆኑም መላው የሀገራችን ህዝቦች፤ በተለይም ደግሞ የበዓሉ ታዳሚዎች የኢሬቻ በዓል ከሚፈቅዳቸው ስነ-ስርዓቶች ውጪ ግጭት የሚቀሰቅሱ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፡ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ አባ ገዳዎች፣ የኢሬቻ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴዎች፣ይህንን በዓል በደመቀ ሁኔታና በሰላም እንዲከበር የምታስተባብሩ ፎሌዎች፣ቄሮዎች፣በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች፣በተለይም ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና የወጣቶች ፌዴሬሽን፤ፖሊስ የሚሰጠውን መመሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲያልቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የበዓሉ ተሳታፊዎች በዓሉን ስታከብሩ የተለየ እንቅስቃሴ ስትመለከቱ በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ትብብራችሁን እንድታደርጉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተማ ያለምንም የፀጥታ ስጋት በሰላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ያደረጉ መሆኑን እየገለፅን በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የደስታ እንዲሆንልን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ይመኛል፡፡

መልካም በዓል!

Report Page