#ETH

#ETH


ፖሊስ በአዲስ አበባና ባሕርዳር ከተሞች በተፈፀመው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ግድያ የተጠረጠሩ ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩን ጨምሮ በአምስት ተጠርጣሪዎች ላይ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ጠየቀ።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ በትክክል ስራውን እያከናወነ ባለመሆኑ የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባና ባሕርዳር ከተሞች ከተፈፀመው ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ በእነ አበበ ፋንታ መዝገብ በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ችሎት በቀረቡበት ወቅት ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ለአራተኛ ጊዜ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍትሐዊነት የለውም ሲሉ ተከራክረዋል።

የጋዜጠኛ ኤሊስ ገብሩ ጠበቆች ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመስራት ያቀረባቸው ተግባራት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለችሎቱ ሲያቀርባቸው የነበሩ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ሊያስጠረጥረው የሚያስችል በቂ መረጃ ሳይኖር በቁጥጥር ስር መዋሉ፣ በማሕበራዊ ሚዲያ ጻፈ ተብሎ የቀረበው የግል አስተያየቱ በመሆኑና፤አስተያየቱንም ባለስልጣናቱ ከተገደሉ በኋላ ያሰፈረው በመሆኑ በውንጀሉ ሊያስጠይቀው አይገባም በማለት ፍርድ ቤቱ በነፃ ሊያሰናብተው ይገባል ብለዋል።

በሕገ- መንግቱም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ያልተከለከለ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይሕንን ሊያጤነው ይገባል ሲሉ አመልከተዋል።

በዚሁ መዝግብ ተጠርጣሪ ከሆኑት መካከል የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወይዘሮ ደስታ አሰፋ ሚስት በመሆናቸው ብቻ በተፈፀመው ወንጀል ሊጠረጠሩ አይገባም፤ ወንጀል ውርስ አይደለም በባለቤታቸው ጥፋት መጠየቅ የለባቸውም ሲሉ ጠበቃቸው ተከራክረዋል ።

ፌዴራል ፖሊስ “በወይዘሮ ደስታ ቤት ተገኘ ብሎ ያቀረበው የጦር መሳሪያ” ባለቤታቸው ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው በወቅቱ የክልሉ ባለስልጣን በመሆናቸው ቤታቸው ያስቀመጡት መሆኑንም አስርድተዋል።

በባለቤታቸውና በእርሳቸው የባንክ ደብተር የተገኝው 150 ሺህ ብር እንዲሁም በግል አካውንታቸው የተመዘገበው 50 ሺህ ብር ሰርተው ያፈሩት ገንዘብ እንደሆነ ጠበቃቸው አንስተዋል።

ምንም እንኳን በተጠርጣሪዋ ወላጅ እናት ስም የተገዛ ተሽከርካሪ ቢኖርም ለሽብር ወንጀል ውሏል የሚል ማስረጃ አልቀረበም ደንበኛቸውም ለ18 ዓመታት በውጭ አገራት በቆዩበት ወቅት ያፈሩት ሃብት እንዳላቸው ነው ለችሎቱ ያስርዱት።

በዚሁ መዝገብ የሚገኙት አቶ አበበ ፋንታን ጨምሮ ሶስት ተጠርጣሪዎች በበኩላቹው ከባለሰልጣናቱ ግድያ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንደሌለበት ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል።

ከሽብር ወንጀል ጋር በተያያዘ ስልጠና ወስደዋል ተብሎ በፖሊስ መጠርጠራቸው አግባብነት የሌለው መሆኑን ጠቁመው ከፀጥታ አካሉ ጋር በመተባበር ማሕበረሰቡን ታገለግላላችሁ ተብለው ለ2 ወር ከ10 ቀን ክልሉን በሚመራው አካል መመልመላቸውንና ስልጠና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናውን በክልሉ በጀት ነው የወሰድነው በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል በመሆኑ በዚህ ጉዳይ መጠየቅ ካለበት ክልልሉን እየመራ ያለው አካል መሆን አለበት ሲሉም አንስተዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ እስካሁን በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ከመረጃ ደሕንነት፣ ከባንክና ከሌሎች ተቋማት በከፊል ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ለችሎቱ ገልጿል።

በቀጣይም የቴክኒክና የሰነድ ማሰረጃዎችን መሰብሰብ፣ የቀሪ የምስክሮችን ቃል መቀበልና ያልተያዙ ግብረአበሮችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ አከናውናለሁ ብሏል።

በተጨማሪም የባንክ እስቴትመንቶችን የመሰብሰብ ወይም የገንዘብ ዝውውሮችን የማገናዘብና የማጣራት ተግባር የሚቀረኝ በመሆኑ የምርመራ ጊዜው በወንጀል ሕጉ 652/200 መሰረት ሊፈቀድልኝ ይገባልብሏል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።

Via #ENA

Report Page