ETH

ETH

TIKVAH MAGAZINE

በሳውዲ አረቢያ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ስደተኞች አያያዝ በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባካሄደው ምርመራ ሦስት ኢትዮጵያዊያን መሞታቸውን በእስር ቤቶቹ ካሉ ስደተኞች ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

አምነስቲ ጨምሮም የሳዑዲ መንግሥት ስደተኞቹ ያሉበት አደገኛ ሁኔታ እንዲያሻሽል እንዲሁም ነጻ እንዲወጡ ጠይቋል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥትም የስደተኞቹ አያያዝ እንዲስተካከል ግፊት እንዲያደርግና ፈቃደኛ የሆኑትም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረግበትን መንገድ እንዲፈልግም ነው ያስታወቀው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ በበኩላቸው  የኢትዮጵያ መንግሥት በስደተኛ ማቆያ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ጉዳይ ሪፖርቶች ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ ጀምሮ እየተከታተለ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ የሚገልጹ ሪፖርቶች በሚወጡ ጊዜም ጉዳዩን ለሳዑዲ ባለስልጣናት በማሳወቅ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ከመጠየቅ ተቆጥበው እንደማያውቁም ተናግረዋል።

አምነስቲ ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደተናገሩት ለሁለት ሆነው በሰንሰለት መታሰር፣ በታሰሩበት ክፍል ውስጥ እንዲጸዳዱ መደረግ፣ ለ24 ሰዓታት በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ ማድረግን ጨምሮ በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ የመከራ ሕይወትን እየመሩ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በገለልተኛ ሁኔታ ለማረጋገጥ አልቻልኩም ያላቸው ቢያንስ የአራት ኢትዮጵያውያንን ሞት መስማቱን አመልክቷል።

በእስር ቤቱ ውስጥ ባለ በሽታ፣ የምግብና ውሃ ችግር እንዲሁም የህክምና አገልግሎት አለመኖር ለሞት የሚዳረጉትን ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ሪፖርቱ ጠቅሷል።

Report Page