#ETH

#ETH


የኢህአዴግ ውህደት የህዝቦችን እኩል የሀገር ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ነው - አቶ ሙስጠፌ መሀመድ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ ለሶስት አስርት ዓመታት የዘለቀ የግንባርነት ጉዞ ከአለም ሀገራት ስልጣን ይዘው በግንባርነት ረጅም አመታትን ከቆዩ ጥቂት የፖለቲካ ድርጅቶች ተርታ አሰልፎታል።

ኢህአዴግ በዋነኝነት በአራቱ ማለትም ህወሃት፣ አዴፓ፣ ኦዲፒና ደኢህዴን አባል ድርጅቶች የተዋቀረ ሲሆን፥ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሀረሪ፣ የጋምቤላ፣ የሶማሌና የአፋር ክልሎች ገዢ ፓርቲዎች አጋር ድርጅቶች ተብለው የተሰየሙለት ግንባር ነው።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግንባርን በትግል ስልትነት ተጠቅመው ስልጣን ከተያዘ

በኋላ ወደ ፓርቲነት ተቀይሮ ሀገር ማስተዳደር በተሻለ አማራጭነት ይቀመጣል።

ከሩብ ምእተ አመታት በኋላ ኢህአዴግም ከግንባር ወደ ፓርቲነት የሚቀየርበትን ስልት ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ከተሰማ ወራት መቆጠር ጀምረዋል።

ይህ በተግባር ሲመነዘር የመጀመሪያ የሚመልሰው ጥያቄ አጋር በሚል ስያሜ የተገደበውን የህዝቦች የስልጣን ባለቤትነት መብትን ነው።

ይህ ጥያቄ በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የመጀመሪያ ድጋፋቸውን ካሳዩ ክልሎች መካከል የሶማሌ ክልል ተጠቃሽ ነው።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የኢህአዴግ አባል መሆን ግድ ነበር ይላሉ።

የአራቱ ፓርቲዎች አባል ያልሆነ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ከዚህ ሀሳብ ተገልሎም ነበር በማለት፥ ይህም በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት ዜጎች እንዲኖሩ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢህአዴግ ውህደት ውስጥ ሌላው መልስ ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ለምን ብሄርን ብቻ መሰረት ያደረገ አካሄድ ይኖራል የሚለውም ነው።

የአስተሳሰብ ልእልና በኢህአዴግ ውስጥ ዋጋ እንዳልነበረው የሚናገሩት አቶ ሙስጠፌ፥ ከዘር ባለፈ ሀሳባዊ አንድነት የሚስተናገድበትና በሀሳብ ልእልና ውሳኔዎች የሚወሰኑበት ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው።

አሁን የመጣው የውህደት አቅጣጫም ይሄን በተጨባጭ የሚመልስ ተራማጅ ሀሳብ መሆኑን አቶ ሙስጠፌ ያነሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያነሱት እንደነበረውም በኢህአዴግ ውህደት የሚፈጠረው አዲስ ፓርቲ ሁሉም እኩል የሚስተናገድበት ፓርቲ ይሆናል።

ይህ የሀሳብ ልእልና ሊስተናገድበት የሚችል እንደሆነ እምነታቸውን የገለጹት የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሀመድ፥ በጥናት የተደገፈው የኢህአዴግ የውህደት ጉዞ በደንብ ውይይት ተደርጎበት ወደ ተግባር የሚገባ በመሆኑ የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጥ እንደሚሆን እምነታቸውን አስቀምጠዋል።

አሁን ላይ ወደ መጨረሻው ምእራፍ እየተጠጋ የሚገኘው የኢህአዴግ ውህደት ከብዙሃኑ በጎ ምላሽ እየተንጸባረቀበት ቢሆንም ለመቃውም የሚሞክሩ አካላትም አልጠፉም።

እንደመከራከሪያ ከሚቀርቡ ነጥቦች አንዱ “የመጨፍለቅ አላማን ያነገበ ነው” የሚል ነው።

አቶ ሙስጠፌ እንደሚሉት ኢህአዴግ ይተች ከተባለ በግንባር ባለበት አቋሙ የአጋር ድርጅቶቹን ህልውናም ሆነ መብት እንደተቋም እየገደበ ያለ በመሆኑ ነው።

ሁሉም ክልል በፌደራል ስርዓቱ የራሱ ነፃነት አለው ያሉት አቶ ሙስጠፌ፥ ይህንን ሀሳብ የሚደግፉ ተራማጆች ወደላይ እንዲወጡ ያግዛል እንጂ ይጨፈልቃል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የእንጨፈለቃለን ሀሳብን የሚያነሱት ለምን የበላይ አንሆንም ከሚል ስሜት የመጣ

እንደሆነ ያነሱት አቶ ሙስጠፌ፥ ምንግዜም ወደተሻለ ምእራፍ ጉዞ ሲጀመር ጥቂቶች ሊያጡ የሚችሉትን ጥቅም ብቻ በማሰብ እንቅፋት መሆናቸው የተለመደ እንደሆነም አብሯርተዋል። እነዚህ ወገኖች የሚያቀርባቸው የመቃወሚያ ነጥቦች ይኖራሉ ያም አያስገርመኝም ብለዋል።

አሁን ግንባሩን ወደ ውህደት አምጥቶ ፓርቲ ለማድረግ የተጀመረው ስራ በተለይ አጋር በሚል ስያሜ የተገደበው የህዝቦች መብት ዋስትናን እንደሚያገኝ ነው የተናገሩት።

Via #FBC

Report Page