#ETH

#ETH


የጸጥታ ችግር በተከሰተበት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ አካባቢ ዛሬ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የክልሉ ሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በጭልጋና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም ችግሩ እልባት እንዲያገኝ እየጠየቁ ነው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ለአብመድ ዛሬ ማምሻውን ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃለፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው ችግር አንጻራዊ ሰላም ታይቶበታል ብለዋል፡፡ በአካባቢውና በጸጥታ ሀይሉ ላይ ጥቃት ሊያደርስ የነበረው የጥፋት ሀይልም አልተሰካለትም ነው ያሉት፡፡ አካባቢው ዛሬ በአንጻሩ ተረጋግቷል ያሉት አቶ አገኘሁ ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

በአካባቢው አሁንም ድንገተኛ ጥቃት የሚያደርሱ ሀይሎች መኖራቸውንና የክልሉ መንግስት ጥፋተኞችን ለመያዝ ጥረት እያደረገ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ “የጥፋት ሀይሉ ዋና ዓላማው የመተማ – ጎንደር መንገድን ዘግቶ ባለሀብቶች ምርታቸውን በወቅቱ እንዳይሰበስቡ እና ለገበያ እንዳያደርሱ በማድረግ በኢኮኖሚ ማዳከም ነው፣ በዚህ ደግሞ አንደራደርም፤ በአጭር ጊዜ መንገዱ ክፍት ይሆናል” ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡ ኅብረተሰቡ ከጥፋት ሀይሉ መላቀቅ እንደሚፈልግና ሰላም ወዳድ እንደሆነ እያሳዬ እንደሆነም ነው ቢሮ ኃላፊው የተናገሩት፡፡ ጥፋተኛውን ለመያዝ እየተሠራ እንደሆነና የሕዝቡን ጥያቄም በሰላማዊና በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ አገኘሁ አስረድተዋል፡፡

በልዩ ሀይሉና በመከላከያ ሰራዊቱ መካከል የቅንጅት ክፍተት እንደነበር ያነሱት አቶ አገኘሁ በጋራ በመገምገምና የጋራ ኮሚቴ በማቋቋም ከወትሮው የተሻለ ቅንጅት እንደተፈጠረም ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ሀይሉም ጥፋት እንዳይደርሰ በትዕግስት እየተጠባበቀ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ ግጭቱ እንዳይበርድ የሚፈልጉ አካላትና የመገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን፣ ግጭቱም በሌሎች አካላት ድጋፍ ያለው መሆኑ መረጋገጡንም አቶ አገኘሁ አስረድተዋል፡፡ የሚዲያ አካላትም ትክክለኛውን መረጃ እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አጀንዳው የአማራን ሕዝብ የማዳከም ነው ያሉት አቶ አገኘሁ የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህን አውቆና አጀንዳ ከመቀበል ወጥቶ ሕዝቡን ከአጀንዳም ነጻ እንዲያደርግም ነው የጠየቁት፡፡

አጀንዳ ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና በቅርብም ለመንግስትና ለሕዝብ ግልጽ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡ ወጣቱም ከስሜታዊነት ወጥቶ በትዕግስት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Via አብመድ

Report Page