#ETH

#ETH


መስቀል የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር መገለጫነቱን በተግባር በሚያሳይ መልኩ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን ላዕላይ ማይጨው ወረዳ በድምቀት ተከበረ።

በዕለቱም የተጣሉ 90 ሰዎችን በማስታረቅ በዓሉ የሰላም እና የፍቅር መሆኑን በተግባር ተመልክቷል።

በላዕላይ ማይጨው ወረዳ በዓሉ በድምቀት የተከበረው ጥንታዊው አቡነ ጰንጠሊዎን ገዳም በሚገኝበትና በተለምዶ “ምሽላም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።

በየዓመቱ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ የተጣሉ ሰዎች በገዳሙ የሚታረቁ ሲሆን በትናንትናው በዓልም በተመሳሳይ 90 የተጣሉ ሰዎች እርቅ ማውረዳቸውን በገዳሙ የእርቀ ሰላም ኮሚቴ አስታውቋል።

በወረዳው ምሽላም እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት መምህር ገብረማርያም ዘሞ እንዳሉት በክረምቱ በተለያዩ ምክንያቶች በአካባቢያቸው ከሚኖር አንድ ግለሰብ ጋር ጥል ውስጥ ገብተው እንደነበረና በአሁኑ ወቅት የመስቀል በዓልን ሲያከብሩ እርቅ በማውረዳቸው ውስጣዊ ሰላም ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

“መስቀል የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል ስለሆነ ቂም ይዘን ማክበር የለብንም ብለን ታርቀን፤ አሁን በመካከላችን ሰላም ወርዷል” ሲሉም ገልጸዋል።


ሌላው የእዚሁ አካባቢ ነዋሪ አቶ ቅዱስ አለሙ በበኩላቸው “በተለያየ ምክንያት በሰዎች መካከል ጠብ ሊከሰት ይችላል፤ በመስቀል በዓል ግን እርቅ በማውረድ ወደሰላም እንዲመጡ ተደርጓል፤ ይህ ጥሩ ልምድ ስለሆነ በቀጣይም ሊጠናከር ይገባል” ብልዋል

ጠብን በፍቅርና በሰላም ማሸነፍ ተገቢ መሆኑን የገለጹት አቶ ቅዱስ፣ በሰዎች መካከል የሚፈጠረውን ቅሬታ በይቅርታ በማለፍ ሰላምንና አንድነትን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

በአቡነ ጰንጠሊዎን ገዳም የእርቀ ሰላም ኮሚቴ አባል የሆኑት መልአከ ሰላም በርሀ በበኩላቸው እንዳሉት፣ መስቀል የፍቅርና የሰላም ተምሳሌ በመሆኑ በየአመቱ በመስቀል በዓል የተጣሉ ሰዎችን የማስታረቅ ስራ በገዳሙ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኮሚቴው በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም የሚያውኩ ነገሮች በመከታተል እና የተጣሉ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ በማስታረቅ በጎ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ላለፉት 5 ዓመታት የተጣሉ ሰዎች በማስታረቅ ብዙዎችን ወደሰላምና አብሮነት ማምጣት እንደተቻለም መልአከ ሰላም በርሀ ተናግረዋል።

“በገዳሙ የሚደረገው የእርቀ ሰላም ስራ የሚበረታታ እና ለሌሎች አካባቢዎች አርአያ የሚሆን ነው” ያሉት ደግሞ የአካባቢው የፖሊስ ኮሚኒቲ አባል ሳጅን ተስፋይ ዘርአይ ናቸው።

ጸብ ውስጥ የገቡ ሰዎች ወደክስ እና ፍርድ ቤት ሳይሄዱ በራሳቸው እርቅ ማውረዳቸው የፖሊስን ሥራ እያቃለለው መሆኑንም ሳጅን ተስፋይ ተናግረዋል።

በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከዚህ በጎ ተግባር ልምድ በመቅሰም የአካባቢው ሰላምና ልማት ለማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም አስገንዝበዋል።

#ENA

Report Page