#ETH

#ETH


‹‹የአማራን ክልል የጦርነት አውድማ ለማድረግ የሚጥሩ አካላት አይሳካላቸውም፤ ይህን ለማድረግ የሚመጡ ካሉም ለመከላከል አቅሙ፣ ብቃቱም አለን፡፡›› አቶ አገኘሁ ተሻገር

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋና አካባቢዋ በተፈጠረ የፀጥታ መደፍረስ ችግር የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ ከወራት በፊትም በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ ዜጎች ለወራት በስደተኛ መጠለያ ውስጥ እንዲቀመጡም ተገደዋል፡፡

ይህ ችግር ተቀርፎ በክልሉ መንግሥትና ያገባኛል ባሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በተደረገ ርብርብ ተስፋ የሚሰጥ ሠላም ተፈጥሮ ነበር፡፡ ዜጎችም አጥተውት ወደነበረው የሞቀ ቤታቸው ተመልሰው መኖር ከጀመሩ የወራት ዕድሜ ብቻ ነው የተቆጠረው፡፡ ነገር ግን ግጭት በድጋሜ አገርሽቶ ከቀናት ወዲህ በተፈጠረ አለመግባባት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡

በዚህ ጉዳይ ለአብመድ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል የሠላምና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ‹‹በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጭልጋ አካባቢ በተፈጠረ ችግር የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ መንግሥት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሠራ ባለበት ወቅት ነው ችግሩ የተፈጠረው›› ብለዋል፡፡ ኃላፊው እንደገለጹት ግጭቱ እገዛ በሚደረግላቸው ሠላም በማይወዱ አካላትና በፀጥታ ኃይሉ የተፈጠረ እንጂ በሕዝብ መካከል አለመሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ሠላም የማይወዱ ክልሉ የጀመረውን የሠላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ የማይፈልጉ አካላት አሉ›› ያሉት አቶ አገኘሁ ችግሩን ለሚቀሰቅሱ አካላትም ድጋፍ የሚያደርግ አካል መኖሩን አመልክተዋል፡፡ አቶ አገኘሁ እንደተናገሩት ጥቃቱ እየደረሰ ያለው በፀጥታ ኃይሉና ትራንስፖርት እየተጠቀሙ ባሉ ንጹኃን ዜጎች ላይ ነው፡፡ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ጥረት እያረገ እንደሆነና የክልሉ ልዩ ኃይል አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠራ እንደሚቆይ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ እንደ አማራ ክልል የማንነት ጥያቄ የተመለሰበት ክልል የለም›› ያሉት አቶ አገኘሁ የቅማንት የማንነት ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት ምላሽ ማግኘቱን፣ የአስተዳደር ጥያቄውንም ለመመለስ በክልሉ መንግሥት እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ችግር እያደረሱ ባሉ አካላት ላይም ከማኅበረሰቡ በመነጠል የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ የፌደራል መንግሥት ድጋፍ እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ የአማራ ክልል ላይ ያነጣጠሩ አሉ፤ የአማራን ክልል የጦርነት አውድማ ለማደረግ የሚፈልጉ ካሉ አይሳካለቸውም፡፡ ከሕዝቡ ጋር እንታገላቸዋለን፤ ለማተራመስ የሚመጣ ካለም ለመመለስ ብቃቱም አቅሙም አለን›› ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፡፡ ችግሩን የሚፈጥሩት አካላትን ጨምሮ ከሚመለከተው አካል ጋር ውይይት በማድረግ ለመፍታት ዝግጁነት መኖሩንም ነው ያመለከቱት፡፡ ግጭቱ የሁለቱ ሕዝቦች እንደሆነ አድርጎ የሚቆጥር አካል አለ፤ ይህ በፍጹም ውሸት ነው፡ ጭቁኑ ሕዝብ ሠላም ወዳድ ነው፤ ችግሩ ሠላም የማይፈልጉ አካላት ከፀጥታ ኃይሉ ጋር የፈጠሩት አለመግባባት ነው›› ብለዋል፡፡

የችግሩ ጠንሳሾች አንዱ ዓላማ የጎንደር መተማ መንገድ እንዲዘጋ ማድረግ መሆኑን ያስረዱት አቶ አገኘሁ መንገዱ በቅርብ እንደሚከፈትና ችግሩም በአጭር ቀን በቁጥጥር ስር እንደሚውል ነው ያስታወቁት፡፡ የተፈጠረውን ችግር እንዲቆምና አካባቢው ወደነበረበት ሠላም እንዲመለስ ወጣቱ ድጋፍ እንዲያርግም አቶ አገኘሁ ጠይቀዋል፡፡

ምንጭ፦ አብመድ

Report Page