#ETH

#ETH


በወላይታ ሶዶ ከተማ ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ከ2 ሚሊዮን 400 ሺ ብር በላይ የመንግስት ገንዘብ በመመዝበር በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ፡፡

ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የመንግስትን ገንዘብ ወደግል ሂሳብ ሲያዛዉሩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወላይታ ሶዶ ዲስትሪክትና ነዋሪዎች ባደረሱት ጥቆማ ፖሊሲ ያዝኳቸው ያላቸው ከ22 በላይ ግለሰቦች በከተማ አስተዳደሩ የመንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ ያሉ ናቸው፡፡

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ስነ-ምግባር ኦፊሰር አቶ ቶማስ ገብረየሱስ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ሃሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ተገቢ ያልሆነ የአትክልትና ማሳ ግምት፤ ገማች ባለሙያና ተቀባይ በማዘጋጀት ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የመንግስት ገንዘብ በመመዝበር ወንጀል የተጠረጠሩ ናቸው፡፡

ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ወንጀሉን በማቀናበር እጃቸዉ ያለባቸዉ ግለሰቦችን በህግ ጥላ ስር በማዋል የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከተማ አስተዳደሩ ማህበረሰቡን በማሳተፍና የምርመራ ቡድን በማቋቋም ተግቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ዉለዉ  የዕምነት ክህደት ቃላቸዉን ከሰጡ በኋላ ከተመዘበረው ገንዘብ ውስጥ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ተመላሽ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

”በህዝብም ሆነ በመንግስት ዕምነት ተጥሎባቸዉ በስልጣን ደረጃ የነበሩ ግለሰቦች የፈጸሙት ከባድ የሙስና ወንጄል በመሆኑ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል” ብለዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኢንስፔክተር ህያዉሁን ሞጋ እንደገለጹት ወንጀሉ ተፈጸመ ከተባለበት መስከረም 3 ቀን 2012 ጀምሮ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተጀምሯል፡፡

እንደ ኢንስፔክተሩ ገለጻ ከመንግስት ሂሳብ ከፍተኛ ገንዘብ ወደግል ሂሳባቸዉ እያዛወሩ ነዉ በሚል በደረሳቸዉ ጥቆማ መነሻ ተጠርጣሪዎችን መያዝ የጀመሩ ሲሆን ከ22 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን አስታዉቋል፡፡

የክስ መዝገባቸዉ ተደራጅቶ የፍርድ ሂደት ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በከባድ የሙስናና ምዝበራ ወንጄል ከተጠረጠሩ ግለሰቦች መካከል አራት ያህሉ በመሰወራቸው ፖሊስ ከፍተኛ ክትትል እያደረገ መሆኑንም ጦቁመዋል፡፡

ወንጀልን በመከላከል ረገድ ሠላምና የህግ የበላይነት እንዲጠናከር የአከባቢው ነዋሪ እያደረገ ያለው ጥረት ከጊዜ ወደጊዜ ከፍ እያለ በመምጣቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

Via #ENA

Report Page