#ETH

#ETH


የመስቀል በዓል ዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለዩን በጋራ ተግባብተን መኖርን የተማርንበት ዕለት በመሆኑ በድምቀትና ታላቅ ኩራት ልናከብረው ይገባል ሲሉ የባህርዳር ሀገር ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ገለጹ።

በየዓመቱ መስከረም 17 የሚከበረው የመስቀል በዓልን አስመልክቶ የሚካሄደው የደመራ ስነ-ስርዓት በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕመናንና የውጭ አገራት ቱሪስቶች በተገኙበት በባህርዳርና በሌሎች ከተሞችም በድምቀት ተከብሯል።

አቡነ አብርሃም በበዓሉ ላይ ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት ወቅቱ የመስቀሉ ባለቤት የሆኑ ክርስቲያኖች ፈተና የበዛበት በመሆኑ ይህን አስከፊ ጊዜ በትዕግስት ዕንጂ ጥፋትን በጥፋት በመመለስ መሆን እንደማይገባው ተናግረዋል።

ህዝበ ክርስያኑ በሃማኖቱና ሃገሩን መጠበቅ እንዳለበት ያሳሰቡት አቡነ አብርሃም የመስቀል በዓል ሲከበር በቤተክርስቲያ ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ለማስወገድ በአንድነትና በመፈቃቀር የሚጸለይበትና ህብረት የሚገለጽበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አለም ታደሰ በበኩላቸው እንደገለጹት የመስቀል በዓል የአንድነትና የተስፋ ምልክት በመሆኑ ህዝቡም ከመለያየትና ከመጥበብ አስተሳሰብ ለመውጣት ታላቅ ትምህርት ተሞክሮ የሚያስተላልፍ በዓል ነው።

አሁን በተጀመረው ለውጥ ህዝበ ክርስቲያኑ አንድነቱና እስከ አሁን ያሰያውን የመተሳሰብና የመፈቃቀር ስሜት ይበልጥ በማጎልበት ለአገራዊ እድገትና ብልጽግ የበኩሉን እንዲወጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“የከተማ ማአስዳደራቸውም ከህዝበ ክርስቲያኑና ከሌሎች እምነት ተከታቶች ጋር በመሆን ባህርዳር የቱሪዝም ማዕከል ሆና እንድትቀጥል ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል” ብዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከልም ወይዘሮ ጥሩሰው አዱኛ እንዳሉት መስቀል ለሰው ልጅ ሁሉ ፍቅር የተሰበከበት ዕለት በመሆኑ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ወጥተዋል።

“በዓሉን ስናከብርም በየአካባቢው የሚስተዋለውን የልዩነት ግድግዳ በመናድ በምትኩ ፍቅርና መተሳሰብን በማስፈን እንዲሆን ሁላችንም መስራት ይኖርብናል” ብለዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ተዋቸው የኔሰው በበኩላቸው “የመስቀል በዓልን ስናከብር የሀገር አንድነትን በማስጠበቅና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባዋል”ብለዋል።

ስለሆነም ህዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር የመስቀሉ ትሩፋት የሆነውን መፈቃቀርና መዋደድ በቀጣይነት በመተግበር አርዓያ ሆኖ መገኘት እንዳለበት ተናግረዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል በአማራ ክልል ደሴ፣ደብረብርሃን፣ደብረማርቆስና ሌሎች ከተሞችም የእምነቱ አባቶችና ምዕመናን በተገኙበት በድምቀት የተከበረ ሲሆን በላሊበላና በጎንደር ከተሞች በነገው እለት የሚከበር ይሆናል።

Via #ENA

Report Page