#ETH

#ETH


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የደመራ በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተከበረ፡፡

በአዲስ አበባ በተከበረው የደመራ በዓል ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እህት ቤተክስቲያን ከሆነችው ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የመጡ የሀይማኖት መሪዎች ፣ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የሀይማኖት ተካታዮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የደመራው ስነ ስርዓት ወደ ተካሄደበት መስቀል አደባባይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ አድባራት የሰንበት ተማሪዎች፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች በተለያዩ ዝማሬዎች ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡

በተመሳሳይ በዓሉ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ፣ አሰላ፣ ወለንጪቲ ፣ ሻሸመኔ እና በሌሎች የክልሉ ከተማዎች የሀይማኖት መሪዎች፣ የሰንበት ተማሪዎች እንዲሁም የሀይማኖት ተከታዮች በተገኙበት ተከብሯል፡፡

በዓሉ በአማራ ክልል ባህርዳር፣ ራያ ቆቦ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ፣ ፍኖተ ሠላም ፣ እንጂባራ ከተማ እና በሌሎች ከተሞች የተከበረ ሲሆን በነገው ዕለተም በጎንደርና ግሸን ደርበ ከርቤ የደመራ በዓል የሚከበር ይሆናል፡፡

የደመራ በዓል በደቡብ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታዮች በተገኙበት ተከብሮ ውሏል፡፡

በደቡብ ክልል ሀዋሳ ፣ አርባ ምንጭ፣ ዲላ ፣ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ እና በሌሎች የክልሉ አከባቢዎች የደመራ በዓል በድምቀት ተከብሯል፡፡

የደመራው በዓል በትግራይ ክልል መቐለ እና አዲግራት በርካታ ህዝብ በተገኘበት ተከብሯል፡፡

በመቐለ በነበረው የደመራ በዓል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ የሀይማኖት መሪዎች እና የሀይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት ነው የተከበረው፡፡

በተመሳሳይ በዓሉ በድሬ ዳዋ ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በድምቀት ተከብሮ መዋሉን ከአከባቢዎቹ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Via #FBC

Report Page