#ETH

#ETH


የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ተዋህዶ አንድ ወጥ ሃገራዊ ፓርቲ ይሆናል እየተባለ የሚነገረውን ጉዳይ ህወሓት ፈጽሞ እንደማይቀበለው የህወሓትና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ በመዋሃድ "የኢትዮጵያ የብልጽግና ፓርቲ" ይሆናል እየተባለ የሚነገረውን ጉዳይ በተመለከተ የግንባሩ መስራችና እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የድርጅቱ ቁንጮ ሆኖ የቆየው ህወሓት ያሉ ችግሮች መፍትሄ ሳያገኙ እንደማይቀበለው አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

በስፋት እየተነገረ ስላለው የግንባሩ ውህደት ጉዳይን በተመለከተ የህወሓትን አመለካከት ሲገልጹ "እንደዚህ ዓይነት ለስልጣን ተብሎ የሚፈጠር ውህደት ህወሓት ፈጽሞ አይቀበለውም" ብለዋል።

ጨምረውም "ህወሓት እንደ መርህ የሚከተለው ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዴት ይቆዩ የሚል ሳይሆን፤ አንድን ድርጅት፣ ድርጅት የሚያደርገው ሃሳብን ነው ብሎ ነው የሚያምነው።"

ይፋዊ መግለጫ መውጣቱን እንደማያውቁ የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ "ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ሩጫ እየተካሄደ መሆኑን አውቃለሁ" ሲሉ ይናገራሉ።

አክለውም ባለፈው በተካሄደው የግንባሩ ስብሰባ ወቅት ውህድ ፓርቲ የመፍጠር ጉዳይ ተነስቶ እንደነበር አስታውሰው "የተባለው ውሁድ ፓርቲ ስለተባለ ብቻ መፈጠር የለበትም" ተብሎ፤ የዓላማ አንድነት በአባል ፓርቲዎች መካከል ተፈጥሯል ወይ የሚል ጥያቄ በህወሓት ተነስቶ እንደነበር ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው እንደሚሉት "በየእለቱ እርስ በርስ እየተናቆሩ የሚውሉት አባል ፓርቲዎችን ይዘን የሃገር ችግርን በመረዳትም ሆነ ችግርን ለመፍታት በምንከተለው መንገድ ጭምር እርስ በእርሱ በሚጋጩበት ሁኔታ ውሁድ ፓርቲ ለመመስረት መሯሯጥ፤ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የሃገሪቷን ችግር የሚፈታ ሃገራዊ ፓርቲ ይፈጠራል ብሎ ህወሓት አያምንም" ብለዋል።

በአባል ፓርቲዎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ መጠራጠርና የዓላማ አንድነት መጥፋት የሚወገድበት መንገድ መፈለግ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ ጌታቸው፤ ግንባሩ በስብሰባው ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዲፈለግ ተስማምቶ እንደነበረም አውስተዋል።

ነገር ግን ከዚያ በኋላ ችግሮች ከመባባሳቸው ባለፈ የተሻሻለ ነገር እንደሌለ አቶ ጌታቸው "የነበረው ውስጣዊ ልዩነት አሁን የበለጠ ሰፍቶ ካልሆነ በስተቀር መፍትሄ አላገኘም" በማለት ይናገራሉ።

ለምሳሌም በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል ከዚህ በፊት የነበረው ልዩነት ተባብሶ መቀጠላቸውን እንጂ መሻሻላቸውን የሚያሳዩ ነገሮች አለመኖራቸውን "የነበሩት ችግሮች ተፈትተዋል ብለን አናምንም" በማለት ተናግረዋል።

የድርጅታቸውን አቋም አጠንክረው ሲገልጹም "ከዚያ ውጪ ካልተዋሃድን ወይም ስያሜ ካልቀየርን በቀጣዩ ምርጫ አናሸንፍም በሚል ርካሽ ስልጣን ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ አካሄድን ህወሓት ድሮም አይቀበለውም አሁንም የሚቀበለው አይሆንም" ሲሉ ፈርጠም ብለው ተናግረዋል።

የድርጅታቸውን ፍላጎት ሲያስቀምጡም ከዚህ በፊት በግንባሩ ስብሰባዎች ላይ እንደተወያዩት አባል ፓርቲዎቹን የሚለያዩዋቸውን ጉዳዮች በማጥበብ በሃሳብ ወደ አንድ የሚያመጣችውን መንገድ መፈለግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ይህ በሌለበት ሁኔታ ወደ ውህደት የምንሔድበት ምክንያት አይታየንም።"

አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት ውህደትን በተመለከተ የተናገሩት ጉዳይ ይፋዊ መግለጫ በተሰጠበት ጉዳይ ላይ እንዳልሆነና እንዋሃዳለን የሚል ይፋዊ ውሳኔም እርሳቸውም ሆነ ድርጅታቸው እንዳልሰሙ አመልክተዋል።

"አሁን እኔ የተናገርኩት ግን ህወሓት ውህደትን የሚረዳበትን አግባብ ነው" ካሉ በኋላ "ህወሓት በዘፈቀደ ለስልጣን ማርኪያ ተብሎ በግለሰቦች የሚደረግን ማናቸውንም ድራማ አይቀበልም" ሲሉ ተናግረዋል።

Via #BBC

Report Page