#ETH

#ETH


ቀን 09/01/20212 ዓ.ም

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ስራ ትምህርት ቤት

አዲስ አበባ

ጉዳዩ ፡- የክፍያ ጭማሪን ይመለከታል

  እኛ የ2012 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እጩ ተመራቂ የማስተርስ ፕሮግራም ተማሪዎች የ2010 ዓ.ም. ሦስት ተርሞችን በECTS ብር 323 ከፍለን መማራችን ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ሥራ ት/ቤት በ2011 ዓ.ም. ያሉ ተርሞችን በECTS ብር 400 ወይም የ24% ጭማሪ ሲያደረግ ትምህርት ከጀመርን በኋላ መሆኑ እንዲሁም ምንም አይነት ዝግጅት እንድናደርግ ቀድሞ ሳይነገረን ቢሆንም፤ ጭማሪው በዛው ያበቃል በሚል የተጨመረውን ክፍያ ያለምንም ተቃውሞ ተቀብለን ከፍለን ተምረናል፡፡ 

ነገር ግን ይባስ ተብሎ ልክ በዓመቱ ለመመረቂያ ጽሑፍ (Thesis) በECTS ብር 600 እንድንከፍል የተወሰነው የገንዘብ መጠን በECTS የ200 ብር ወይም 50% ጭማሪ ሲያስከትል፤ ከመጀመሪያው ዓመት የክፍያ ተመን ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ወደ 86% ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

እኛ እጩ ተመራቂ ተማሪዎችም የጭማሪው መጠንና ድግግሞሽ በማየት ለአገሪቱ አርአያ እንዲሆን ከሚጠበቅበት የመንግስት ከሆነው አንጋፋ ተቋም የወጣ የክፍያ ጭማሪ ትዕዛዝ ነው ብሎ ለመቀበል በእጀጉ ተቸግረናል፡፡

 እኛ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የተደረገብን ከፍተኛ ጭማሪ ቢያንስ በሚከተሉት ምክንያቶች ተገቢ ነው ብለን አናስብም፤

የጽሑፍ ስምምነት ባይኖረንም፤ ተቋሙ ከተማሪዎች ጋር በፈጠረው የተግባር ግንኙነት (De facto) ሕጋዊ ውል ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም ያለተማሪዎቹ ስምምነት ሁለት ግዜ አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በተግባር የተመሠረተውን ውል በመጣሱ፤

በማንኛው የሕግ አሠራር፤ አንድ የአሠራር ማሻሻያ ሲተገበር ተፈፃሚነቱ (Effective Date) ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት በገቡ ተማሪዎች ላይ የነበሩ አሠራሮችን (የክፍያ ማሻሻያዎችን) ወደኋላ ተመልሶ ስለማይተገበር፤ ይተግበር ከተባለም ተማሪዎች ወይም ተወካዮቻቸው ጋር መስማማት አስፈላጊ በመሆኑ፤ 

አሁንም ድረስ ተቋሙ ለክፍል ትምሕርቶች በECTS ብር 400 እያስከፈለ፤ ለመመረቂያ ጽሑፍ (Thesis) ግን በECTS ብር 600 ማስከፈሉ የማናውቀው አሠራር እንዲሁም እርስ በራሱ የሚጋጭና አመክንዮ የሌለው በመሆኑ፤

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ኢትዮጵያ በከፍተኛ የዋጋ ንረት እግር ተወርች ተይዛ ባለችበት ሁኔታና መንግስትም ይኽንን ከፍተኛ ችግር ለመቅረፍ ሌት ተቀን በሚሠራበት ጊዜ፤ በምርምር ሥራው የአገሪቱን ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከሚጠበቀው አንጋፋ ተቋም፤ ይባስ ብሎም ይኽ የተጋነነ ጭማሪ በመንግስት ከሚተዳደር ተቋም አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡  ጭማሪው ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ አመክንዮ የሌለው በመሆኑ፤  ካለንበት ወሳኝ ምዕራፍ አንፃር፤ ትምሕርታችንን ከመቀጠል ውጭ ሌላ አማራጭ የማይሰጥ የጭማሪ ውሳኔ ማሳለፋችሁና ከተማሪው ምንም አይነት ውይይት እንዲሁም ስምምነት ባለማግኘታችሁ፤ ጭማሪውን በግዳጅ (Duress) የተገኘ የሚያደርገው በመሆኑ፤

የተማሪዎች ገቢ በጭማሪው ልክ የሚያድግ ባለመሆኑ፤ አያሌ ተማሪዎችም ሥራ ሳይኖራቸው እንደሚማሩ ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም አገራችን ውስጥ ባለው ሁሉን አቀፍ የዋጋ ንረት ተማሪዎችን ጨምሮ የበርካታ ኢትዮጵያዊያን የዕለት ተዕለት ኑሮ በእጅጉ እየተፈተነ በመሆኑ፤  

ባጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች መሰል ምክንያቶች ውሳኔያችሁን በመከለስ ወደነበረበት የክፍያ ምጣኔ እንድታስተካክሉት በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከሰላምታ ጋር

Report Page