#ETH

#ETH


በድሬዳዋ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት አንድ ሰው «በተባራሪ ጥይት» መገደሉን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። በግጭቱ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን እና በውል ያልታወቀ ንብረት መዘረፉን የአስተዳደሩ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ተወካይ ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ ተናግረዋል። 

በድሬዳዋ ደቻቱና አምስተኛ ከተባሉ አካባቢዎች ተነስቶ ወደ ሌሎች እየተስፋፋ በመጣው ግጭት ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ሲወድም የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የአስተዳደሩ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ከሃምሳ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጿል። 

የአስተዳደሩ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ተወካይ ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት "ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ በከተማው የተቀሰቀሰውን ግጭት የሃይማኖትና የብሄር መልክ ለማስያዝ እንዲሁም ባንኮችን ለመዝረፍ የተደረገው ሙከራ በፀጥታ ኃይሉ እና በህብረተሰቡ ትብብር ሳይሳካ ቀርቷል። ይሁን እንጂ ሀብት ተዘርፏል ግምቱ ያልታወቀ የኅብረተሰቡ ንብረት ወድሟል" ብለዋል። አቶ ሚካኤል፦ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ቁጥሩ በውል ባልታወቀ ነዋሪ ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንና አብዛኞቹ በህክምና ተቋማት ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል። የአንድ ሰው ሕይወት በተባባሪ ጥይት ማለፉንም አስረድተዋል። አቶ ሚካኤል ከመስከረም አንድ ዋዜማ አንስቶ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ ከሀምሳ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።  የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ለማስከበርና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዟል ያሉት አቶ ሚካኤል ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የሚጠረጠሩ አካላትን በሕግ ቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እንደሚሰራ ገልፀው በዚህ ሂደት ጉዳዩ ሳይመለከታቸው የተያዙ ካሉ በማጣራት ነፃ የሚሆኑበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል።

በፀጥታ ኃይሉ የቅርብ ክትትል አንፃራዊ መረጋጋት ቢታይበትም ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመ ሁኔታው ያልተመለሰውን ሰላም ለማረጋገጥ በቀጣይ ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ይደረጋል ተብሏል። ይሁን እንጂ በርካታ ሰዎች አለአግባብ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው፤ የፀጥታ ኃይሉም ተገቢውን የሕግ የማስከበር ርምጃ በወቅቱ እየወሰደ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች በመቅረብ ላይ ናቸው። 

Via DW

Report Page