#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ያለበትን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክተው በጽ/ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 68 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ የኮርቻ ቅርፅ ግድቡ ግንባታ 96 በመቶ መድረሱን ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

በቅድሚያ ኃይል የሚያመነጩት ሁለት ዩኒቶች (early generation units) (ዩኒት 9 እና 10) ከዚህ በፊት የነበረባቸውን የብረታ ብረት ሥራዎች የብየዳና የማቴሪያል አጠቃቀም ችግር ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ የተከላ ሥራቸውን 50 በመቶ ማድረስ መቻሉን በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱን ዩኒቶች ከ2013 ዓ.ም አጋማሽ በኃላ ወደ ኃይል ማመንጨት ሥራ ለማስገባትም ዕቅድ ተዘጋጅቶ በጥብቅ ክትትል እየተመራ እንደሚገኝም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለፁት፡፡ ለቅድመ ማመንጨት ሥራው የሚያስፈልጉ ተርባይኖች የሚገጠሙበት የስፓይራል ኬዝ ተከላ እና የብየዳ ሥራዎች ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛሉም ተብሏል፡፡

በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች መዘግዬት ተቀዛቅዞ የቆዬው የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ የተጀመረ ሲሆን የኃይል ማመንጫ፣ የስዊች ያርድ፣ የጎርፍ ማስተንፈሻ እና የኮርቻ ቅርፅ ግድብ የሲቪል ሥራዎች በሙሉ አቅም በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ዶ/ር አብርሃም አስታውቀዋል፡፡

በግድቡ የግራ ክፍል ግድቡን ከባህር ጠለል በላይ 560 ሜትር ከፍታ ላይ ለማድረስ 26 ሺህ ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት ተሞልቷል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በቀሪው የግድቡ ክፍል ላይ ደግሞ 50 ሺህ ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት የመሙላት ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ለታችኛው የውሃ ማስተንፈሻ (ቦተም አውትሌት) ሥራ የሚያስፈልገውን ማቴሪያል ከውጭ ሃገር በማስገባት በሳይት ላይ የምርት ሥራ መጀመሩም ታውቋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የጎርፍ ማስተንፈሻ 96 በመቶ፣ የኃይል ማመንጫ ክፍል 70 በመቶ እንዲሁም የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት 80 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም ማሳየት እንደቻሉ ዶ/ር አብርሃም ተናግረዋል፡፡

በግድቡ የውሃ አሞላል እና በሚለቀቀው የውሃ መጠን ዙሪያ ግብጽ ያቀረበችው የተለዬ አቋም የግንባታ ሥራውን ወደ ኋላ እንደማያስቀረውም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሥራው በ2003 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ዓመታዊ አማካይ የኃይል ምርት አቅሙም 15,670 ጊጋ ዋት ሰዓት ነው፡፡

መስከረም 13/2012 ዓ.ም

Report Page