#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሚዲያ መግለጫ

ስለ ኮሚሽኑ ለውጥ እና የሲዳማ ሁኔታ ምክክር በሐዋሳ ከተማ፡

+++++++++++++++++++++++++++++++++++++

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ከመስከረም 7-9 ቀን 2012 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ የሚገኘውን አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ እና ራዕይ ተከትሎ በኮሚሽኑ ውስጥም ስለሚደረገው የለውጥ መርሃ-ግብር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር ለማድረግ ሲሆን፤ በዚሁ አጋጣሚም በሐዋሳ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ እስረኞችንና የአያያዛቸውን ሁኔታ ጐብኝተዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ የክልሉ ምክር ቤቶች አፈ ጉባዔዎች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ሚዲያም ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ከሐዋሳው ጉብኝት አስቀድሞም በግጭቱ ከተጐዱ ቤተሰቦች ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ እንዳሉት “ በግጭቱ የተጐዱ ሰዎችንና ቤተሰቦችን በተገቢው መጠን ከመርዳት እና መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ የምርመራው በፍጥነት መጠናቀቅ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል፡፡”

ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን እና ሌሎች ምንጮችም በተገኘው መረጃ መሠረት እስከ አሁን በተደረገው የፖሊስ ምርመራ፤ በሶስት ማዕከሎች በእስር ይገኙ ከነበሩ ወደ 1500 ገደማ እስረኞች ውስጥ ከግማሽ በላይ የተለቀቁ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በጋራ እያካሄዱ ባሉት የምርመራ ሥራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር እንዲለቀቁ ማስቻሉ ጥሩ እርምጃ መሆኑን፤ ነገር ግን “ ለችግሩ መነሻ የሆነው ዋናኛ ምክንያት በሲዳማ ዞን ም/ቤት ለቀረበው የክልልነት ጥያቄ በሚመለከታቸው አካላት ሲሰጥ የነበረው ምላሽ ወቅታዊ እና ስልታዊ አለመሆንና በሌላ በኩል ጥያቄውን በተናጠል ውሳኔ እና በኃይል ጭምር ለማስፈፀም የፈለጉ ቡድኖች በአራመዱት አስተሳሰብ የተነሳ በተፈጠረው የፖለቲካ ውጥረት እና ቀውስ በመሆኑ፤ አሁንም በህዳር ወር 2012 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ ከታቀደው ሕዝበ-ውሳኔ አስቀድሞ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች በማዘጋጀት፤ እንዲሁም ተአማኒ በሆነ የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስቀድሞ መግባባት ላይ በመድረስ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር እጅግ አፋጣኝ እርምጃ ይሻል ” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ አበክረው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በአዲስ መልክ በማደራጀት እና በማጠናከር ነጻ የሰብዓዊ መብት ተቋም አድርጐ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት፤ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በየደረጃውና በየክልሉ የሚደረገው ምክክር እንደሚቀጥልም ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

Report Page