#ETH

#ETH


የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል!

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሃል ክፍል የአርማታ ሙሌት ስራ መጀመሩን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ከFBC ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።

የሁለቱ ቅድመ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የብረታ ብረት ገጠማ እና ኤሌክትሮ መካኒካል ስራም ግማሽ ተጠናቋል ነው ያሉት። የግድቡ አካል ከሆኑት አንዱ የሆነው ኮርቻ ግድብ (ሳድል ዳም) ግንባታው ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል። አሁን ላይ ግድቡ ከ16 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ አለት የተሞላ ሲሆን፥ ኮንክሪት ለብሶ የማጠናቀቂያ እና የለቀማ ስራ ላይ መድረሱንም ገልጸዋል።

የግድቡ ሌላኛው አካል የሆነው ዋናው ግድብም በግራ እና በቀኝ በኩል የሚጠበቀው 145 ሜትር ከፍታ ላይ የደረሰ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት የግድቡ የመሃል ክፍል አርማታ ሙሌት ስራ ተጀምሯል። ለታችኛው የውሃ ማፈሳሻ ቦይ የሚያገለግሉ ብረቶች ከውጭ ሃገር የገቡ ሲሆን፥ ከአንድ ወር በኋላም የገጠማ ስራው እንደሚከናወን አስረድተዋል።

አሁን ላይ ግድቡ አጠቃላይ ግንባታው 68 ነጥብ 3 በመቶ የደረሰ ሲሆን፥ በቀጣዩ አመትም 750 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል። ከሁለት ሳምንት በፊት የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አል ሲ ሲ፥ ግድቡ ግንባታው የተጀመረው ግብፅ በፖለቲካ ቀውስ በተመታችበት ወቅት ነው የሚል ሃሳብ መሰንዘራቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩም የፕሬዚዳንቱ ንግግር ህዝብን ለማሳመን የቀረበና የተለመደ መሆኑን በመጥቀስ፥ በግድቡ የግንባታ ሂደት ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይፈጥር አስረድተዋል። የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል።

Via #FBC

Report Page