#eth

#eth


ከካናዳ መጥቶ የሞተው የ 10 ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ እድለኛው ሚካኤል ገብሩ ቀብር ተፈጸመ፡፡

• "ስለሚካኤል አሟሟት በቂ መረጃ አላገኘንም" ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ

ቤተሰቡ ነገሩ አስደንጋጭ ዱብእዳ እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ የ 41 አመቱ ሚካኤል ገብሩ የዛሬ ሁለት አመት ነበር በሚኖርበት ካናዳ ቶሮንቶ የ 10.7 ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ እድለኛ የሆነው፡፡ የካናዳ ዜግነት የነበረው ሚካኤል ህይወቱ በአንድ እድል ተለውጦ መልቲ ሚሊየነር ቢሆንም በማግኘቱ ጠባዩ ያልተቀየረ ሌሎችን ለመርዳት ደግ የነበረ ሰው ነበር ይላሉ ወዳጅ ዘመዶቹና የሚያውቁት ሁሉ፡፡

ለራሱ ያደረገው ነገር አልነበረም ሌላው ቀርቶ ቤት እንኳ የገዛው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው ሲሉ የሚናገሩት ቤተሰቦቹ ላለፉት ሁለት አመታት ለሌሎች እንጂ ለራሱ አንድ ነገር ሳያደርግ ኖሮ የማይኖርበትን ቤት ገዝቶ ነው ይህን አለም የተሰናበተው ሲሉ በሀዘን ስሜት ለሲቢሲ ዜና አውታር ስለ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

ሎተሪ ባገኝ የተቸገሩ ሰዎችን ነው የምረዳበት ሲል የሚመኝ ደግ ሰው ነበር የሚሉት እና በቅርበት የሚያቃውቁት ሎተሪ ከወጣለት በኋላ እንኳን በአካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና ለቤተክርስቲያናት ብዙ ልገሳ አድርጓልም ይላሉ፡፡

ሲመኝ የኖረው ሎተሪ ወጥቶለት ቱጃር ከሆነ በኋላ ማንነቱንና ባህሪውን ሳይቀይር በወዳጅ ዘመዶቹና በሚያውቃቸው እንደተወደደ መኖሩን ብዙዎች መስክረውለታል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ወደናፈቃት ትውልድ ሀገሩ ተጓዘ፡፡ ሆኖም በድንገትና ሳይታሰብ ባለፈው ሳምንት መሞቱ ተሰማ፡፡ ቅዳሜ እለት በኖረበት ካናዳ ወዳጅ ዘመድ በቤተክርስቲያን ተሰባስቦ በጸሎተ ፍትሀት ተሰናበተው፡፡ ሰኞ (ዛሬ ማለት ነው) በተወለደባትና በድንገት ባረፈባት ኢትዮጵያ ግብአተ መሬቱ መፈጸሙን ሲቢሲ ዘግቦታል፡፡

የዜና ምንጩ ያነጋገራቸው ቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ የሚካኤል አሟሟት ሁኔታ ግልጽ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ያገኙት የተብራራ መረጃ እንደሌለ፤ የካናዳ ኤምባሲም ሆነ የሚመለከታቸው የአሟሟቱን ሁኔታ በዝርዝር እንዳላስረዷቸው ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ወዳጆቹ ደግሞ ሚካኤል ምናልባትም ባገኘው ገንዘብ የተነሳ የሰዎች ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡ ሲቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ እንደጠየቀ ቢገልጽም የካናዳ ኤምባሲም ሆነ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ እንደሚሰጡ ከመግለጽ በዘለለ ያሉት እንደሌለ በመጥቀስ ነው የትውልደ ኢትዮጵያዊያዊው ሚካኤልን አሟሟት ታሪክ የደመደመው፡፡

ሲቢሲ የዜና አውታር ይሄንን ቢልም አዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዩን በተመለከተ ከ3ቀን በፊት የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን በፌስ ቡክ ገጹ መግለጹ ይታወሳል፡፡

እንደ ፖሊስ ሪፖርት መስከረም 3 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 6 ሰዓት በአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ፒያሳ ልዩ ቦታው መሀሙድ ሙዚቃ ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአቶ ሚካኤል አጽበኻ ገብሩ ላይ የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 2 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የጠቆመው የአ/አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ብዛታቸው 3 የሆኑ ተጠርጣሪዎች በዕለቱ ሟች ሚካኤል አፅበኻ ከጓደኛቸው ጋር እየተዝናኑ ከቆዩ በኋላ ወደ ማደሪያቸው ለመሄድ ታክሲ እየጠበቁ በነበሩበት አጋጣሚ ንብረት ለመዝረፍ በማሰብ ጉዳት አድርሰውባቸው ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡ ያለ ሲሆን ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱን በ05/01/2012 ዓ.ም ማምሻውን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑንና ቀሪውን አንድ ተጠርጣሪ ለመያዝ ክትትሉ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡

Via #SHEGERTIMES

Report Page