#ETH

#ETH


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የ2011 ዓ.ም የዕረፍት ወራት ከክረምቱ ተሰናብቶ ሄዷል። አሁን ደግሞ 2012 ዓ.ም ከሙሉ ዕድልና ደስታጋር በአደይ አባባ ፍካትና በምድር ገጽታው አረንጓዴ ልምላሜ አስደናቂ ውበት ተላብሶ ወደ አዲሱ የትምህርት ዘመን ይጋብዛችኋል። እንኳን ለዚህ አዲስ ዘመን አደረሳችሁ።

ነባርና አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ተስፋንና አዲስ ኃይልን ሰንቀው ወደ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሲያቀኑ ከማየት የሚበልጥ ደስታ ወልደው ላሳደጉ ወላጆችም ሆነ ለእኛ ለሁላችን ሊኖር አይችልም። ለምንወዳት አገራችንም ቢሆን ልጆቿ ሲማሩና ሲመራመሩ ከማየት በላይ ተስፋ የሚያሰጣትና ደስታ የሚያጭርባት ነገር አይኖርም፡፡ ትምህርትን ፍለጋ ከአገር ወደ አገር የመንከራተት ዘመን ታልፎ፣ ትምህርት ራሱ ካለንበት ቀዬና ከተማ ድረስ ከሚመጣበት ዘመን ላይ ለመድረስ ውድ አገራችሁና ሕዝቦቿ ብዙ ዋጋን ከፍለዋል።

በሁሉም የአገራችን ቋንቋዎችና ባህሎች የትምህርትንና የዕውቀትን ጥቅም የሚገልጡ አባባሎች መኖራቸው ሕዝባችን ምን ያህል ለዕውቀት ዋጋ እንደሚሰጥና ሊቅን እንደሚወድና እንደሚያከብር ምስክር ነው።

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪ አስተሳሰቡ ዓለም አቀፋዊ፣ ተልዕኮው አገራዊ ነው፡፡ ውድድሩም በዋናነት ከራሱና ከጊዜው ጋር ነው። ራሱንና ጊዜውን ያሸነፈ ወጣት አገሩን ዓለም ከደረሰበት ማዕረግ ከማብቃት ተሻግሮ አገሩን የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ መሪ ለማድረግ የሚተጋ ምሁር ነው፡፡ ውድድሩ ዓለም አቀፋዊ፣ ፉክክሩም የማያቋርጥ ነው፡፡

ተሸናፊው ጠላት ሰው ሳይሆን፣ ድህነትንና ኋላ ቀርነት ነው። የሚሮጠው ዛሬን ሳይጠቀምበት እንዳያልፈው፣ ነገም ሳይዘጋጅ ደርሶበት እንዳያመልጠው ነው። ክፉውን በመልካም ለማሸነፍ እንጂ በጎውን በማጥፋት የተሻለ መስሎ ለመታየት ዕውቀትና ጊዜውን አያባክንም። የዕውቀትና የጥበብ ተገዢ እንጂ ለማንኛውም የአካልና የአእምሮ ሱስ ምርኮኛ አይሆንም።

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪ በሁሉ የሚማር፣ ከልዩ ልዩ ዕውቀት ምንጮች መቅዳት የሚችል የጥበብ ረሃብተኛ ነው። ከተለያዩ ባሕሎች የተለያዩ መላዎችን ለመካን ይተጋል። በየቋንቋዎቻችን የተሰወሩ ልዩ ልዩ ምሥጢሮችን ይመረምራል። ከብዙ ማኅበረሰቦች ዘርፈ ብዙ ታሪኮችና ትውፊቶች ተሰናስሎ የሚሸመነውን ታላቅ አገራዊ ትርክት ለመረዳት ይማስናል። ልዩነትን ያደንቃል፤ አንድነትን ያደምቃል፡፡ ፍቅርን ያጋምዳል፡፡

ከእርሱ የተለየ ወገን ሲያገኝ በፍርሃት ሳይሆን በጉጉት አዲስ የዕውቀት በር ስለተከፈተለት በወዳጅነት በር ዘው ብሎ ይገባል።

የከፍተኛ ትምህርት ተማሪ የአገር አማካይ የትውልዶች ድልድይ መሆኑን ይረዳል፡፡ከኋላ ለሚከተሉት ሕጻናት አርአያ፣ ቀድመውት ለተራመዱ ጎልማሶችና አረጋውያን ደግሞ መከታ መሆኑን ይገነዘባል፡፡

ትናንትናና ነገን በጠንካራ የሥራ ሞራል ዐለት የማገናኘትና በማይበጠስ የፍቅር ሠንሰለት የማስተሣሠር ኃላፊነት እንደወደቀበት ከልብ ያምናል፡፡ የሚመኛትን አገር ለመገንባት፣ የሚፈልገውን ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የሚያስበውን ማኅበረሰብ ለመመሥረት የሚያስችሉት ዕድሎች ሁሉ በእጆቹ ውስጥ እንዳሉና፣ የመድረሻ መንገዶቹም ከትምህርት ቤትና ከሕይወት የሸመታቸው ዕውቀቶች እንደሆኑ በትክክል ይገባዋል። ጊዜና እድል ከእጁ የጨመረለትን መልካም አጋጣሚ፣ በግዴለሽነትና በሞኝነት እንዳያጣው እንደ ዕንቁ ተጠንቅቆ ይጠብቃል።

በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምትገኙ ወጣት የአገራችን ተስፋዎችና ተማሪዎች፣

ኢትዮጵያ በብዝኃነቷም በአንድነቷም ምን እንደምትመስል ለማወቅ ግቢዎቻችሁን ማየት ይበቃል። ደግሞም ትናንት እንዴት እንዳለፍን ትምህርቶቻችሁ በታሪክ ይገልጡላችኋል። ነገ ምን መሆን እንዳለብን በውስታችሁ በተጠነሰሱ ራእዮቻችሁ ልቡናችሁ ያመላክታችኋል፡፡

የአገራችንን ልዩ ልዩ ጸጋዎች እንያዝ። ከትናንቱ በጎ በጎውን ወስደን፣ ክፉውን አርመን፣ የሁላችንንም ጥንካሬ በአንድ አዋሕደን፣ ለመጓዝ ካልቻልን እንዴት መቀጠል ይቻለናል? ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ሰው ይቅርና፣ ለብቻው ደምቆና ገዝፎ መፍሰስ የሚችል አንድም ወንዝ የለም፡፡

የወንዞቻችን ታላቅነት በአንድነት ተደምረውና ተደማመረው በሚፈሱት ዝናብና ምንጭ፣ ኩሬና ጅረት በሚገኘው ውኃ ነው። ዓባይ ከአገር አገር ግንድ ቢያንከባልል፣ ግብጽና ሱዳንን ቀጥ አድርጎ ቢመግብ፣ ምሥጢሩ ያለው ባሮና ተከዜ ጣናና ሌሎች ስማቸውን የማናውቃቸው ብዙ ጅረቶች ተደምረውበት ብርቱ በመሆኑ ነው። ብቻውን ታላቅ የሚሆን የለም፡፡

ከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችንም የመደመር ተምሳሌቶችና የአንድነትን ኃይልና የብዝኃነትን ውበት ማንጸባረቂያ ናቸው። ዩኒቨርሲቲ ማለትም ዩኒ – አንድ እና ቨርሲቲ-ብዙ ከሚል ቃል የተሠራ ነው አንድንና ብዙን የሚያይዘው ምሥጢር ደግሞ የመደመር ኃይል ነው።

ከአላፊው ትውልድ ይልቅ መጪው የእናንተ ትውልድ ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያ ያስፈልገዋል፡፡ ዛሬእንደ ትናንት አይደለም። ባለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን በራችን ዘግተን፣ ከዓለም ርቀንና ተነጥለን መኖር አንችልም። እኛ ባንሄድም ዓለም ራሱ ደጃችን ድረስ ይመጣል፡፡

የያዛችሁት ስልክና ከቤታችሁ ያሉ ቴሌቪዥኖች ይሄንን አስረግጠው ይነግሯችኋል፡፡

አማራጭ ከዓለም ጋር ተወዳድረንና ተባብረን፣ የተሻለን ሆነን በመገኘት አሸንፈን መገኘት ብቻ ነው፡፡ ደካማ አገር ይዘን ጠንካራ ሕዝብ፣ ድኻ አገር ይዘን አሸናፊ ትውልድ ሊኖረን አይችልም፡፡

በገጠር የበጎች ዋና ጠላት ቀበሮ ነው፡፡

ቀበሮ ወደ በጎች በረት ራሱ መግባት ካቃተው መጥፎን ጠረኑን በነፋስ ትከሻ ይልከዋል፡፡

እርሱ ራሱ ከፍ ያለ ቦታ ይሆንና የነፋሱን አቅጣጫ ተከትሎ እግሩን በማንሣት መጥፎ ጠረኑን ወደ በጎቹ ይልካል፡፡ በጎቹ በቀበሮው መጥፎ ጠረን ተደናግጠው መጀመሪያ በረታቸውን ያምሱታል፡፡

ቀበሮው ያለበትን አቅጣጫና ቦታ ከማወቅ ይልቅ ሲተራመሱ እርስ በርሳቸው መተማመናቸው ይጠፋል፡፡ በመጨረሻም እርስ በርሳቸው በቀንዳቸው ይዋጋሉ፡፡

ከዚያም በረታቸውን ሰብረው በገዛ እጃቸው ለቀበሮው ተንኮል ሲሳይ ይሆናሉ።

እናንተም በአንድ ላይ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማህበር የምትኖሩ የዕውቀት ባልንጀሮች እንደ በጎቹ የዋሕ መሆን የለባችሁም፡፡ ሰላማችንንና ዕድገታችንን የማይፈልጉ በቀበሮ አስተሳሰብ የሚተዳደሩ ብዙዎች አሉ፡፡

እነርሱ በሰላማዊ ቦታ፣ በድሎት ሥፍራ ተቀምጠው ባለ መጥፎ ጠረን የቃላት ዘመቻቸውን ወደ መማሪያ ግቢዎቻችሁ ይልካሉ፡፡ የሐሰት ወሬ፣ የግጭት ቅስቀሳ፣ የብሔር ጥላቻ፣ በየኮሌጆቹ በየማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ይልካሉ፡፡ እርስ በርሳችሁ እንድትጠራጠሩ፣ እንድትከፋፈሉና እንድትበጣበጡ ያደርጋሉ፡፡

በመጨረሻም በገዛ እጃችን ወደ ቆፈሩልን ጉድጓድ ሰተት ብለን እንገባለን። እነርሱ ምንም አይሆኑም። በድኻው ልጅ ሕይወትና ሕልም ግን ይጫወታሉ። ተዋጉ ብለው ከቢጤዎቻቸው ጋር በግፍ በሰበሰቡት ገንዘብ ራት ይገባበዛሉ። ተነሡ ብለው ወደ ምቹ አልጋዎቻቸው ሄደው ይተኛሉ። እናንተን ተሠው፣ ሙቱ ብለው ሰብከው ሲጨርሱ እነርሱ ግን እድሜያቸውን ለመቀጠል ልጆቻቸውን ይዘው ወደ እረፍት ለሽርሽር ይሄዳሉ።

ወጣቶች በፍጹም አትሞኙ።

ማንኛውም ነገር ከማድረጋችሁ በፊት ወላጆቻችሁን፣ ሀገራችሁንና የነገ ተስፋችሁን አስቡ፡፡ እናንተ ግብ ያላቸሁ ወደ አቀዳችሁት ዒላማ የምትገሠግሡ ባለ ሕልሞች ናችሁ፡፡ በተቆፈረለት መንገድ ሁሉ የምትፈሱ የትውልድ ኩሬና የመስኖ ውኃ አይደላችሁም፡፡

ይህ የትምህርት ዘመን ሰላማዊ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ፡፡ በነገዋ ኢትዮጵያ ብሩኅ ተስፋን የምታዩበት ዘመን እንዲሆን እንደ መንግሥት አበክረን እንሠራለን፡፡

የአገራችን ዐቅም በፈቀደው መጠን ፍላጎቶቻችሁን ለማሟላት እንተጋለን። ከዚህ አልፎ ከመሥመር የሚወጣውን በጥባጭ በተገቢ መንገድ ወደ ትክክለኛው መሥመር እንዲመለስ ሕግን የማስከበር ኃላፊነታችንን እንወጣለን፡፡ እያንዳንዳችሁ ሕልማችሁ እንዲሞላና በሰላም ወጥታችሁ በሰላም ወደ ቤተሰቦቻችሁ እንድትመልሱ እንደ መሪያችሁ የሚቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።

የእናንተንም፣ የአገራችሁንም፣ የወገናችሁንም የነገ ሕይወት ለማቃናት – ዕድላችሁ በእጃችሁ፣ መንገዳችሁ በዕውቀታችሁ ላይ ነው፡፡ ያገኛችሁትን ዕድል ለአሰናካዮች፣ የቀሰማችሁትንም ዕውቀት ለጨለማ አበጋዞች

አሳልፋችሁ አትስጡ፡፡ ነገ የምታክሙን፣ የምትመሩን፣ ደህንነታችንን የምታስክብሩልን።ልጆቻችንን የምታስተምሩልንና አገራችንን ወደ ላቀ ደረጃ የምታሻግሩልን እናንተ ናችሁ። እናንተን ማገልገልና ማስተማር ከሁሉ የላቀና የከበረ ሥራ ስለሆነ ይህንን የምናደርገው በደስታ ነው።

አዲሱ የትምህርት ዘመን የዕውቀት ብልጽግና የምትጎናጸፉበት ይሁን፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም



Report Page