#ETH

#ETH


የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የቤት ኪራይ አበል 18 ሺህ ብር ሆነ፤ የማይመልሱት የእጅ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ላፕቶፕ ኮምፒዩተርም ተፈቅዶላቸዋል፡፡

ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በየወሩ 18 ሺህ ብር የቤት ኪራይ አበል እንዲከፈላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወሰነ። በሌሎች ጥቅማጥቅሞች ላይም ማሻሻያ ያደረገ ሲሆን የማሻሻያ መመሪያው ከነሐሴ 01 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።

የከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለመወሰን ሕዳር አንድ ቀን 1997 ዓ.ም የወጣውን መመሪያ ለማሻሻል በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ መሠረት የቤት ኪራይ አበል የሚከፈላቸው ከፍተኛ ኃላፊዎች መንግሥት የመኖሪያ ቤት ማቅረብ ካልቻለ ኃላፊው ቤት እስኪሰጠው ድረስ በየወሩ 18 ሺህ ብር የሚከፈለው ይሆናል።

መንግሥት መኖሪያ ቤት ያልሰጣቸው ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የቤት ኪራይ የሚከፈላቸው በየመስሪያ ቤቱ በጀት ተይዞለት መሆኑን የሚያብራራው መመሪያው ባልና ሚስት ሁለቱም ባለስልጣናት ከሆኑ ግን ጥቅሙ የሚሰጠው ለአንደኛው አካል ብቻ መሆኑን አመልክቷል።

ለከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ለሚመደብ ተሽከርካሪ ፍጆታ የሚውል በወር 245 ሊትር ናፍጣ ወይም 200 ሊትር ቤንዚን መሆኑን መመሪያው ጠቅሶ ለቤተሰብ ለሚመደብ ተሽከርካሪ ደግሞ 200 ሊትር ቤንዚን የሚሰጣቸው ይሆናል። እንዲሁም ኃላፊው መኪናውን በአቅራቢያው የማያሳድር ከሆነም ተሽከርካሪውን ለማሳደር እና ኃላፊውን ለማምጣት የሚኖረውን ርቀት ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ ነዳጅ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊ መፍቀድ የሚችል መሆኑን መመሪያው አመልክቷል።

ኃላፊው ለመኖሪያ ቤቱ ለሚጠቀመው ስልክ በየወሩ እስከ 200 ብር የስልክ ወጪ የሚከፈለው መሆኑን የጠቀሰው መመሪያው ለተንቀሳቃሽ ስልክ ለሚደረግ ግንኙነት የሚያስፈልግ የስልክ አገልግሎት ወጪ ከመስሪያ ቤቱ በመረጃ ተደግፎ በሚቀርብ ጥናት ለገንዘብ ሚኒስቴር በማቅረብ ማስወሰን የሚቻል መሆኑ ተብራርቷል። እንዲሁም የመንግሥት ኃላፊው ለሥራ የሚጠቀምበት ተመላሽ የማይሆን ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ላፕቶፕ ኮምፒዩተር በመስሪያ ቤቱ ለአንድ ጊዜ ተገዝቶ የሚሰጠው መሆኑንም አስታውቋል።

የኢ.ፕ.ድ እንደዘገበው የመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ማለት ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር፣ ዋና ዳይሬክተር እና ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ እንዲሁም በእነዚህ ደረጃ የተሾሙ የበላይ ኃላፊዎች በጥቅማጥቅም መመሪያው የሚካተቱ መሆናቸው ተጠቅሷል።

Via EPA/AMMA

Report Page