#ETH

#ETH


በድሬ ዳዋ ከተማ ቀፊራ እና አዲስ ከተማ በሚባሉ አካባቢዎች ግጭት መኖሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ።

አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ "አምቡላንሶች ሰዎችን ወደ ሆሰፒታል ሲያመላልሱ ነበር። ጉዳት ደርሶባቸው ደም የሚፈሳቸው ሰዎችንም ተመልክቻለሁ'' ብለዋል።

የግጭቱ መነሻ ደግሞ "አዲስ ከተማ ጋራ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ አዲስ በተገነባው የተክለኃይማኖት ቤተ-ክርስቲያን ላይ ሰዎች ድንጋይ በመወርወራቸው ነው'' ብለዋል።

"የአዲስ ከተማ ሰፈር ልጆች ድንጋይ ወረወሩ የተባሉትን ልጆች ደበደቡ ሲባል ነው የሰማነው" ብለዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የፖሊስ አባል እንደተናገሩት ደግሞ "በተሳሳተ ወሬ በቤተ-ክርስቲያኑ ላይ ጥቃት ለማድረስ የቀፊራ ሰፈር ሰዎች መጥተዋል የሚል ወሬ ከተናፈሰ በኋላ ነው ድንጋይ መወራወሩ የተጀመረው" ይላሉ።

"የቀፊራ ልጆች ተክለኃይማኖት ቤተ-ክርስቲያን ላይ ጉዳት ሊያደርሱ እየመጡ ነው የሚል ወሬ ነው የተነዛው፤ ከዚያ የአከባቢው ነዋሪዎች ደግሞ እንዴት ይሆናል ብለው ተነሱ። የሰፈር ጸብ ነው እየተካረረ ያለው" በማለት ይህ የከተማዋ የፖሊስ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በግጭቱ የደረሰው ጉዳት ምን ያክል እንደሆነ የተጠየቁት የፖሊስ አባሉ "በትክክል ይህ ነው ማለት ባልችልም፤ ደንጋይ መወራወር ስለነበረ የተፈነካከቱ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ለህይወት የሚያሰጋ ጉዳት ያጋጠመው የለም" ብለዋል።

የጸጥታ ኃይሎች በቦታው በመገኘት ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የፖሊስ አባሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁን የዓይን እማኝ አሁንም ድረስ (እሁድ ከሰዓት) የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ እና የጸጥታ አካላት በአከባቢው በስፋት እንደሚገኙ ተናግረዋና።

"ግጭት ወዳለበት ሰፈሮች ማለፍ አልቻልንም። ምክንያቱም ሰፈሩ በጠቅላለው በፌደራል ፖሊስ ተወሯል" ሲሉም ተናግረዋል።

በተከሰተው ግጭት በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ከሆስፒታልና ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እንዳልተሳከ ዘግቧል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Report Page