#ETH

#ETH


የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም በዛሬው እለት በ2012 የትምህርት ዘመን አጠቃላይ የትምህርት ዝግጅት ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ነው፡፡

#መግቢያ

ከፍተኛ ትምህርት ለሀገራችን እድገት የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን 50 የመንግስት እና 201 የሚደርሱ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ፡፡ በውስጣቸውም በዓመት እስከ 1,000,000 (አንድ ሚሊዮን) የሚጠጉ ተማሪዎችን እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡

ባለፉት ጊዚያት የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በተደረጉ ጥናቶች የትምህርት ጥራቱ ያለበትን ጉድለት በመለየት ለዚህ መፍትሔ የሚሆን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ በዋናነት 37 ምክረ ሀሳቦች ቀርበው ሀገራዊ ውይይት ተካሂዶ ወደተግባር ለማውረድ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚሁ መሠረት በ2012 የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የሚተገበሩ የለውጥ ሥራዎችና ሰላማዊ የመማር መስተማር ሂደትን የማረጋገጥ ሥራዎችን በሚመለከት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሀ. የ2012 ትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ዓመት ትምህርትን በተመለከተ

በፍኖተ ካርታው ጥናት ምክረ ሐሳብ መሠረት የነባሩን ሥርዓተ ትምህርት ጉድለቶችን የሚሞሉ የጋራ ኮርሶች ተለይተው ለተማሪዎች እንዲሰጡ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ይህም የመጀመሪያ ድግሪ ትምህርት ዝቅተኛ ቆይታ ጊዜን አራት ዓመት አድርጎታል፡፡ ለነዚህም ኮርሶች የሚያስፈልጉ መምህራን ቅጥር በዩኒቨርሲቲዎች በኩል ተካሂዷል፡፡ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከዩኒቨርሲቲዎች በተወጣጡ ነባር መምህራን የማስተማሪያ ሞጁል ተዘጋጅቷል፡፡

ስለሆነም በተከለሰው ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ ሰምስቴር ቅበላ በአራት የቅበላ ዓይነቶች ይሆናል፡፡

እነርሱም፡-

i. በየተፈጥሮ ሳይንስ፣

ii. በተፈጥሮ ሳይንስ በመምህርነት፣

iii. በማህበራዊ ሳይንስና

iv. በማህበራዊ ሳይንስ በመምህርነት ናቸው፡፡

በሁለተኛው ሴሚስተር የተማሪዎችን የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤት መሠረት በማድረግ በአምስት የሙያ መስኮች ምደባ ይደረጋል፡፡

እነርሱም፡-

i. ህግ

ii. ህክምና እና የጥርስ ህክምናምና እና የጥርስ ህክምና

iii. የእንስሳት ህክምና

iv. ፈርማሲ

v. ኢንጂነርንግ ናቸው፡፡

የሌሎቹ የሙያ መስኮች ምደባ የሚደረገው ከአንድ ዓመት የትምህርት ቆይታ በኋላ የተማሪዎችን ዓመታዊ ውጤት መሠረት በማድረግ ነው፡፡

ለ. ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በልህቀት መለየትን በተመለከተ

ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በልህቀት መለየት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የተለያዩ የምርምር ውጤቶች አመላክተዋል፡፡ ከጥቅሞቹም መካከል፡-

i. የተማሪዎችን የፈጠራ አቅም፣ የመማር ብቃት፣ ችሎታና መክሊት በትምህርት ስርዓቱና አሰጣጡ በሚገባ የሚያወጣና የሚያጠናክር ይሆናል።

ii. ምሁራን ወደ አንድ ተልዕኮና ልህቀት ማዕከል እንዲያተኩሩ በማድረግ የተጠናከረ የትምህርት አሰጣጥንና የምርምር ባህል ለማዳበር ያስችላል። ለመምህራኑ ተማሪዎቻቸውን ለመከታተልና ለማማከር የተሸለ ዕድል ይፈጥራል፡፡

iii. የትምህርት ግብዓቶችን በተጠናከረ መንገድ ለየዩኒቨርሲቲዎቹ ለማሟላትና በመንግሥት ላይ የሚኖረውን የበጀት ጫናና ብክነትን ለመቀነስም ያግዛል፤ በሂደቱም ተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት የማግኘት ዕድላቸውን ከፍ ያደርጋል፡፡

iv. ተቋማት ውስጣዊ ልህቀት ማዕከላትን በመገንባት ከሌሎች ከመቅዳት ይልቅ የራሳቸውን ፈጠራ (innovative ideas) እንዲጠቀሙ ያስችላል፤ በአዲስ እውቀትና ቴክኖሎጂ ፈጠራ እንዲልቁም ምቹ መደላድል ይፈጥራል፡፡

v. የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እንደ ዓይነተኛ መሣሪያ ያገለግላል፡፡

vi. አግባብነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ፕሮግራሞችንና ሌሎች ድግግሞሽን በመቀነስ ውጤታማ ሀገራዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር ያግዛል፡፡

vii. የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸውና ውጤታማነታቸው እንዲጨምር ያግዛል፡፡

viii. መንግስት በውስን ሀብት ለሚሰራቸውን ሀገራዊ አጀንዳዎች ቅድሚያ ትኩረት ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ix. ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ምርጫቸው ከፍላጎታቸው ጋር እንዲጣጣም የተሻለ ሰፊ ዕድል ይሰጣል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮና በልህቀት የመለየቱ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ2012 ጀምሮ በሂደት የሚተገበር ይሆናል፡፡

ሐ. ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን የማረጋገጥና የማስቀጠል ሥራን በተመለከተ

ዩኒቨርሲቲዎች በመተሳሰብ በመተባበርና በፍቅር ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖር ጥበብ መሠልጠኛ መድረክ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ራስን ለማሻሻል፣ ቤተሰብን ለማገዝ እና የጋራ ሀገርን ለመገንባትም በርካታ ዕድል የሚሸመትበት ሰፊ ገበያም ናቸው፡፡ በተቃራኒው አልባሌ አመለካከቶችና ተግባራት ላይ ለመውደቅም መጥፎ አጋጠሚዎችም የሚገኙበት ነው፡፡

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ያጋጠሙንን ችግሮች በዝርዝር በመለየት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመፍትሔዎች ዙሪያ በመወያየት ለሁሉም አካላት ኃላፊነት እና ተጠያቂነት የሚያሰፍን አሰራር እንዲተገበር በማድረግ መስራት እንዳለብን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት፡-

1. ተማሪዎች

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ የሚኖራቸው ቆይታ ጊዜ በጣም ውስን ቢሆንም የወደፊት ሕይወታቸውን በመወሰን ረገድ ደግሞ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡ ስለሆነም ተማሪዎች ጊዜ ካለፈ ተመልሶ የማይገኝ ትልቅ ሀብት መሆኑን በማስተዋል በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሙሉ ትኩረታቸውን የላቀ እውቀትና ክህሎት በመሸመት እንዲሁም ራስን በመልካም ስብዕና በማበልጸግ ላይ ቅድሚያ መስጠት የሚጠበቅባቸው መሆኑን እንገልጻለን ፡፡

ስሆነም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለእውቀት ፍልጋ የሚተጉ፣ በሀሳብ ሌላውን የሚሞግቱ፤ በመተባበር፣ በመመካከር እና በመደጋገፍ ለውጤት የሚጥሩ በመሆን ለሌሎች የሀገራችን ወጣቶች በሥነምግባራቸው፣ በመልካም ስብዕናቸውና በአለባበሳቸው አርዓያ እንዲሆኑ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የግልና የጋራ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ የዩኒቨርሲቲውን ህግ አክብረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ በተዘጋጀው የኃላፊነት መውሰጃ ቅጽ ላይ ቤተሰቦቻቸውና ራሳቸው በመፈረም በወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ተረጋግጦ ማህተም ያፈበትን ቅጽ ይዘው በምዝገባ ወቅት መቅረብ ያለባቸው መሆኑን መግለጽ እንወዳለን፡፡

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሌላውን ኃይማኖት፣ ፖለቲካዊ እምነት ወይም ብሔር የሚያጣጥል ወይም የሚያጎድፍ ጽሑፍ ወይም ምልክት ያለባቸውን አልባሳት መልበስ ወይም ቁሳቁሶችን መጠቀም የማይፈቀድና ተጠያቂነትንም የሚያስከትል ተግባር መሆኑን እናሳውቃለን፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ተማሪዎች የዲስፕሊን ጥፋት ላይ ተሳትፈው በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ጉዳት ቢያደርሱ ወይም ለጥፋቱ ተባባሪ ሆነው ብገኙ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የንብረቱን የዋጋ ግምት የሚከፍሉ መሆኑን እናስገንዝባለን፡፡

2. መምህራን

መምህራን ወላጅና ባለአደራ ናቸው፡፡ የተማሪዎች ብሎም የሀገር የተሻለ ነገ ቀያሾች የግንባታውም መሐንዲሶች ናቸው፡፡ በመሆኑም በመልካም አርዓያነት የተሻለ ነገን ለተማሪዎች ለሚያሰይ ተግባርና አመለካከት ስርጸትና ግንባታ ፈር ቀዳጅ ሆነው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ ልረባረቡ ይገባል፡፡

የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎችን ለመቅረጽ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመረዳት ያለምንም የትምህርት ጊዜ መባከን ተማሪዎቹ የሚጠበቅባቸውን እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ከመጣር በተጨማሪ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ በአለባበስ እና በሥነምግባር አርአያ በመሆን ያላቸውን የማይተካ ሚና በተሻለ ውጤታማነት እንዲወጡ አደራ እንላለን፡፡

በተጨማሪም መምህራን በግል የማንኛውም ኃይማኖት ተከታይ የመሆን፣ የፖለቲካ አመለካከት የመያዝ፣ የፈለጉትን የማሰብ፣ የመናገርና የመጻፍ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካ፣ የኃይማኖት፣ የብሔር ወይም የአካባቢ አደረጃጀቶችን አመለካከትና ተግባር በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ማንጸባረቅ፣ ማስተባበር፣ መተባበር የትምህርትን ነጻነት የሚጋፋ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ከነዚህ አስተሳሰቦችና ተግባራት ነጻ እንዲሆኑ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ የሚጠበቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ በተያያዘም መምህራን የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ግንባታ ላይ ያላቸው ጉልህ ሚና የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ሲሆን ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ የጥላቻ ንግግሮችና ጽሑፎች ራሳቸው መቆጠብ ያለባቸው ብቻም ሳይሆን ለሳላማዊ መማር ማስተማር ያለውን አስተዋጽኦ በመገንዘብ ሌሎችንም ልመክሩ የሚገባ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

3. የአስተዳደር ሠራተኞች

ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊና የተረጋጉ ሆነው እንዲቀጥሉ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ የሚሰጡት አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ከአድልዎ የጻዳ እንዲሆን አደራ እንላለን፡፡

በተጨማሪም ችግሮች ሲከሰቱ በመወያየትና በሠከነ መልኩ መፍታትን ባህል ማድረግ እንዲሁም መተባባርን መተሳሰብን እና አብሮ መኖርን የሚያጎሉ ተግባራትን ማከናወን የሚጠበቅባቸው መሆኑን እገልጻላን፡፡

4. የተማሪ ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች

ልጆቻቸው የዩኒቨርሲቲውን ህግና ደንብ አክብረው እንዲንቀሳቀሱና ለሌሎች መልካም አርዓያ እንዲሆኑ የመምከርና ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላም አስፈላጊውን ክትትል የማድረግ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ በተዘጋጀው የሃላፊነት መውሰጃ ቅጽ እንዲፈርሙ ይጠበቃል፡፡

5. የአካባቢው ማህበረሰብና አስተዳደር

ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የመጡ ተማሪዎችን እንደቤተሰብ አካል በመቁጠር በመምከር እና በመንከባከብ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ውጤታማ አንዲሆኑ የበኩላቸውን እንዲወጡ አደራ እንላለን፡፡ በተያያዘም በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሰላምና መረጋጋትን የሚያናጉ እንቅስቃሴዎችን ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በመተባበር የመከላከልና ተከስተውም ሲገኙ ፈጣንና አስተማሪ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ በኩል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሠሩም ይጠበቃል፡፡

የ2012 የነባርና አዲስ ገቢ ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

ነባር ተማሪዎች ከመስከረም 5 እስከ 25

አዲስ ተማሪዎች ከመስከረም 25 – 29/2012 ዓ.ም ይሆናል፡፡

ተማሪዎችን በኤክስትራ ኮ ካሪኩላር ትምህርቶች ከጅምሩ ጀምሮ የሚያሳትፉ ማዕቀፎችም ተዘጋጅተዋል፡፡

ለነባርና አዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላትና የተማሪ ቤተሰቦች እንኳን ለ2012 የትምህርት ዘመን አደረሳችሁ!!

መስከረም 09/2012 ዓ.ም

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ

Report Page