#ETH

#ETH


ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውስኔ ዙሪያ ከደቡብ ክልል የተለያዩ ተቋማት ጋር መወያየቱን አስታወቀ።

ቦርዱ እንዳስታወቀው አስቀድሞ ባወጣው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም መርሀ ግብር መሰረት የተለያየ ሀላፊነት ያላቸው የህግ አስፈጻሚ እና የጸጥታ አካላት እና የቦርዱ የስራ አመራር አባላት የህዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም ሰላማዊነት ዙሪያ ተወያይቷል።

በውይይቱም የፌደራል ፓሊስ ተወካዮች ፣ የደቡብ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ተወካዮች፣ በክልሉ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሀላፊ፣ የአዋሳ ከተማ ፓሊስ አዛዥ፣ የሲዳማ ዞን ፓሊስ ሀላፊ, የክልሉ የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ጽ/ቤት ሃላፊ በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት ቦርዱ ከእለት ተእለት ሰላምና ፀጥታ አጠባበቅ በተለየ የምርጫ ሂደት በራሱ የሚፈልገው የፀጥታ ዝግጅት መኖሩን ገልጾ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ፣ እንዲሁም የድምፅ መስጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የህግ አስፈጻሚ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ለተሳታፊዎቹ አስገንዝቧል፡፡ 

ከተለያዩ ቢሮዎች የተወከሉት የጸጥታ አካላትም በነሱ በኩል ያለውን እይታ ያቀረቡ ሲሆን የዞኑ ሰላምና መረጋጋት እየተሻሻለ መሆኑን ገልጸው በህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና በጋራ እና በተናጠል ሊያከናውኗቸው ስለሚገቧቸው ተግባራትም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም በህዝበ ውሳኔው ዝግጅት፣ ድምፅ አሰጣጥ እና ድህረ ህዝበ ውሳኔው ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን፣ መወሰድ ያለባቸው የመፍትሄ ተግባራትን እና ሃላፊነቱን የሚወስደውን አካል የሚያሳይ የህዝበ ውሳኔ ፀጥታ እቅድ በስብሰባው ተሳታፊ በሆኑት የህግ አስፈጻሚዎቹ ለመስከረም 23 ቀን 2012 ዓ.ም አዘጋጅተው አንዲያቀርቡ መስማማታቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

Via #ETHIO_FM

Report Page