#ETH

#ETH


በምዕራብ ወለጋ መንዲ ከተማ በሚገኝ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ካምፕ ላይ የተወረወረ ቦምብ አንድ ሰው ሲገድል በርካቶችን አቁስሏል።

የመንዲ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለሙ ጉዲና ለቢቢሲ እንደተናገሩት ትናንት ጠዋት (ማክሰኞ) የተወረወረው ቦምብ የአንድ ሰው ህይወት ከመቅጠፉም በላይ በርካቶችን አቁስሏል።

የመንዲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አዳም ኦልጂራ "በቅድሚያ ሶስት ሰዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታላችን መጡ። ከዚያ ደግሞ ህይወቱ ያለፈ ሌላ ሰው መጣ" በማለት ይናገራሉ።

"ህይወቱ ያለፈውም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸው ከቦምብ ፍንጣሪ ይመስላል" ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ቆስለው ወደ ሆስፒታሉ የመጡት ህክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል እንዲወጡ ተደርጓል።

ከቦምብ ፍንዳታው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋለ ተጠርጣሪ እንዳለ የተጠየቁት አቶ አለሙ "እስካሁን አልታወቀም። እያጣራን ነው።'' ሲሉ መልሰዋል።

በምዕራብ ወለጋ የምትገኘው የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ተካልኝ እሁድ ዕለት ማታ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማም በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ከተማ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በዚህ መሰሉ ግድያ ምክንያቶች የነዋሪው ሕይወት ዕለት በዕለት ሰቆቃ የተሞላ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ግለሰቦች አስረድተዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ይህን መሰሉ በነዋሪዎችና በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያ ሲፈጸም ወራት የተቆጠሩ ሲሆን ለጥቃቱ በይፋ ኃላፊነት የሚወስድም ሆነ ተጠያቂ የሆነ አካል አልተገኘም።

ከአንድ ዓመት በፊትም በዚሁ ጉሊሶ ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እና አዋሽ ባንክ በታጣቂዎች መዘረፋቸው ይታወሳል። በወቅቱ መንግሥት የኦነግ ሠራዊት አባላት ዝርፊያውን መፈጸማቸውን አሳውቆ ነበር።

በተያያዘ ዜና በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄር አስተዳደር ልዩ ዞን ባቲ ከተማ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ካምፕ ላይ ቅዳሜ ዕለት ቦምብ ተወርውሮ እንደነበር የዞኑ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሑሴን አህመድ ለቢቢሲ ገልፀዋል ።

ቦምቡን ማን እንደወረወረ የታወቀ ነገር የለም ያሉት አቶ ሁሴን፤ የተወረወረው ቦምብ በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለማድረሱንም ጨምረው ተናግረዋል።

BBC

Report Page