#ETH

#ETH


ለጅማ ዩኒቨርሲቲ የአዲስ አበባ ካምፓስ ተማሪዎች በሙሉ!

ጉዳዩ፡- ተገቢነት በሌላቸው ጽሁፎችና መግለጫዎች እንዳትደናገሩ ስለማሳሰብ፦

ዩኒቨርሲቲያችን መንግስት የከፍተኛ ትምህርትን ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በማሳካት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ያለው መሆኑ ከሁላችሁም የተሰወረ አይደለም፡፡ የመንግስትን የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊነት ከማረጋገጥ አኳያ ዩኒቨርሲቲያችን በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጠውን ትምህርት አድማስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ መምጣቱ የቁርጠኝነቱ አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ይኸውም ዋና መቀመጫው ጅማ ከተማ ሆኖ በአገሪቱ የተለያዩ ስፍራዎችና ከአገር ውጪም በሐርጌሳ ጭምር ካምፓሶችንና የትምህርት ማዕከሎችን ከፍቶ ትምህርቱን በማስፋፋት ላይ የሚገኘውም በዚሁ አግባብ ነው፡፡


ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲያችን የሚያደርገውን ህጋዊ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና ለማስቆም የሚሞክሩ አካላት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተገንዝበናል፡፡ ይኸውም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና ጥቂት የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች በኤጀንሲው የፌስቡክ ገጽ እና በግል የፌስቡክ ገጽ በለቀቋቸው መረጃዎች እንዲሁም የፕሬስ ኮንፈረንስ ጠርተው በመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዩኒቨርሲቲያችንን ስም ሲያጠፉና ሲያቆሽሹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲያችንን ስም ከማጥፋት አልፈው በቁጥር 01/መ-4/2688/11 መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ በአዲስ አበባው ካምፓሳችን በመማር ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች ጥሪ በማድረግ ወደ ሌላ ተቋም እንደሚያዛውሯቸው በኤጀንሲው የፌስቡክ ገጽ መረጃ ለቀዋል፡፡


ነገር ግን ዩኒቨርሲቲያችን የአዲስ አበባውን ካምፓስ የከፈተውም ሆነ ላለፉት ሰባት አመታት ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ሲሰጥ የቆየው ዩኒቨርሲቲውን እንደገና ለማቋቋም በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 አንቀጽ 2(1) እና አንቀጽ 3 መሠረት ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሆኖ ስለተቋቋመ እና ዋና ግቢው ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎች እና የምርምርና የማሕበረሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን የማቋቋም መብት በህግ ስተሰጠው ነው፡፡ የድጋፍ አገልግሎት ከሚሰጥ የግል ተቋም ጋር ህጋዊ ስምምነት ተፈራርሞ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ የአገልግሎት ግብአቶችን በማግኘት ላይ ያለው ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 93(1) ስር ማንኛውም የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ለማድረግ የሚያስችል ህጋዊ መብት እንዳለው በተደነገገው መሠረት ነው፡፡ ይህም ሆኖ በህግ ድንጋጌዉ ላይ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ትርጓሜ እንዲሰጥ ተጠይቆ ዉጤቱን እየተጠባበቅን ባለንበት ወቅት ሁከት ለመፍጠር የሚደረገዉ እንቅስቃሴ አግባብነት የጎደለዉ ነዉ፡፡  


በሌላ በኩል ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ሥልጣንና ተግባር ኤጀንሲው በተቋቋመበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 261/2004 አንቀጽ 6 እና በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 89 ስር የተዘረዘረ ሲሆን በሁለቱም ህጎች ኤጀንሲው ተማሪዎችን ከአንድ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነጥቆ ለሌላ ተቋም ለመስጠትም ሆነ አንድን ካምፓስ ለመዝጋት የሚያስችል ሥልጣንና ኃላፊነት አልተሰጠውም፡፡ ስለሆነም ኤጀንሲውንና የሥራ ኃላፊዎቹ በዩኒቨርሲቲያችን ዙሪያ የሚያደርጓቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተገቢነት የሌላቸዉ እና በሌላቸው ስልጣን የተፈፀሙ በመሆናቸው በህግ የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡

ውድ ተማሪዎቻችን! ዩኒቨርሲቲያችን በአዲስ አበባ ካምፓስ ከፍቶ ለተማሪዎች ትምህርት ሲሰጥ የቆየው በህጋዊ መንገድ መሆኑን እያረጋገጥን ይህንኑ በህግ የተሰጠውን ሥልጣን በመጋፋት ኤጀንሲውና የሥራ ኃላፊዎቹ በማድረግ ላይ ያሉት አግባብ የሌለዉ እንቅስቃሴ ህዝብና መንግስት እንዳይረጋጋ የሚያደርግ በመሆኑ በፅኑ የምናወግዘው ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲያችን እስከ አሁን ድረስ በኤጀንሲው በበላይ የሥራ ኃላፊዎች ሲፈፀሙ የነበሩትን አግባብነት የሌላቸዉን ተግባራት በትዕግስትና በሰከነ መንፈስ ሲከታተልና መፍትሄ ሲያፈላልግ የቆየ ሲሆን፣ የአሁኑ ተግባር ግን የዩኒቨርሲቲውን ህልውና የሚፈታተንና የኤጀንሲውን የስልጣን እና ሃላፊነት ገደብ የጣሰ በመሆኑ፣ ዩኒቨርሲቲያችን ጉዳዩን ከሚመለከታቸው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመወያየት መፍታትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ተግባራትን ለመፈፀም ቁርጠኛ አቋም የያዘ መሆኑን እየገለፅን፣ በኤጀንሲው ጥሪ ሳትረበሹና ሳትሳሳቱ ዩኒቨርሲቲዉ ከተማሪ እና ከወላጅ ተወካዮች ጋር ባደረገዉ ዉይይት መሰረት ጉዳዩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አዉቃችሁ በትዕግስት እንድትጠብቁን እናሳስባለን፡፡

 

ከሠላምታ ጋር!


ግልባጭ፡-

 

o ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ 

o ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣

o ለሚኒስትሮች ምክር ቤት፣

o ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

o ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣

o ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ 

 አዲስ አበባ 


- ለፕሬዘዳንት ጽ/ቤት

- ለአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት

- ለአስተዳደርና የተማ/አገል/ም/ፕሬዘዳንት

- ለቢዝ/ልማት ም/ፕሬዘዳንት

- ለምር/የማህበ/አገል/ም/ፕሬዘዳንት

- ለዋናው ሬጂስትራር ጽ/ቤት

- ለርቀትና ተከታ/ትምህርት ዳይሬክቶሬት

- ለዉጭ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ

     ጅማ ዩኒቨርሲቲ

Report Page