#ETH

#ETH


በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን የኦሮሚያ ክልል አመነ!

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ፣ በጉጂና በቦረና እንዲሁም በአንዳንድ የሐረርጌ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የኦነግ ታጣቂዎች እና ለታጣቂዎች ስንቅ እና መረጃ አቀብላችኋል የተባሉ በርካታ ግለሰቦች ተይዘው በምርመራ ላይ መሆናቸውን የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ታዬ ደንደአ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ አረጋገጡ።

እንደታዬ ገለፃ፣ ተጠርጣሪዎችን የመያዝና የማሰር እንቅስቃሴዎች በክልሉ አንዳንድ ዞኖች እንደነበሩ ጠቅሰው፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ በአራቱም የወለጋ ዞኖች እና በጉጂ የሚገኙ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከንቲባዎችና ከፍተኛ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ሃያ ዞኖች ውስጥ በዘጠኙ ዞኖች ከስድስት ሺ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል ሲል ለአዲስ ማለዳ መግለፁን ተከትሎ አቶ ታዬ ቁጥሩ ተጋኗል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

‹‹ለሠራዊቱ መረጃና ስንቅ ሲያቀብሉ የነበሩ በርካታ ሰዎች በወለጋና በጉጂ ዞኖች ታስረዋል›› ያሉት ታዬ ‹‹ፓርቲዎችን ኢላማ ያደረገ እስር የለም፣ ሁሉም እየተነሳ የፓርቲዬ አባል ታስሯል እያለ የሚያወራው ለፖለቲካ ጥቅም ነው›› ሲሉ ተችተዋል። አገርን ለማረጋጋት በሚደረጉ ጥረቶች ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለምርመራ መቅረባቸው እንደ አዲስ ነገር መታየት የለበትም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የክልሉ መንግሥስት ፓርቲዎቹን ለማጥቃት ያደረገው ዘመቻ ቢሆን ኖሮ የራሱን ከፍተኛ አመራሮች ባላሰረ ነበር ብለዋል።

‹‹በርካታ እስረኞች ከኹለት ወር በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በእስር ላይ ይገኛሉ›› ሲል ፓርቲው ቅሬታውን በተደጋጋሚ ሲያሰማ መቆየቱ ይታወሳል።

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በወለጋ በሚገኙ አራት ዞኖች፣ በቦረና፣ ጉጂ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ በሚገኙ የጦር ካምፖች ውስጥ ታስረው ከሚገኙ አባላቶቹ ውስጥ አብዛኞቹ ፍርድ ቤት አልቀረቡም። የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ሲጠየቅም በነቀምት፣ በጊምቢ፣ በገሊላ ወረዳ ሊሙና በጉጂ ዞን በርካታ የኦፌኮ አመራሮች “ኦነግ ናችሁ” የሚል ምክንያት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በርካታ የኦነግ ታጣቂዎች በፈቃዳቸው እጃቸውን መስጠታቸውንና ሌሎችም በቁጥጥር ስር በመዋላቸው በአካባቢው መረጋጋት በመስፈኑ በርካታ እስረኞች ጉዳያቸው እየተጣራ በመለቀቅ ላይ ናቸው ሲሉ ታዬ ይሞግታሉ።

አዲስ ማለዳ በምዕራብ ጉጂ የሚገኘው የኦፌኮ ጽሕፈት ቤት፣ በአካባቢው ባሉ ኮማንድ ፖስት አመራሮች መበርበሩንና በጽሕፈት ቤቱ የነበረውን አባላቸውን ደብድበው ራቁቱን ጥለውት መሔዳቸውን ከኦፌኮ ያገኘውን መረጃ ዋቤ አድርጋ መዘገቧ አስተውሷል።

በወቅቱ የተፈጠረውን ችግር ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ቶሌራ አደባ በበኩላቸው፣ አባሎቻቸው በምሥራቅ ሐረርጌ፣ ጅማ፣ ኢሊባቦርና ወለጋ እየታሰሩ መሆናቸውን ገልፀው ድርጊቱን ለኦሮሚያ ክልልና ለፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ቢያስታውቁም፣ እናጣራለን፤ ይስተካከላል ከሚል ምላሽ ባለፈ አንድም ማስተካከያ አለመደረጉን አስታውቀው ነበር። ታዬ በእስረኞቹ ቁጥር፣ ስላሉበት እስር ቤትና የክስ ሁኔታቸው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ምንጭ፦ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ



Report Page